የጸጋው ፍሬያማነት

 

ፍሬያማ በሆነ አገልግሎት ውስጥ የእግዚአብሔር ጸጋ

 

በኤፍ. ዋይኒ ማክ ሌዎድ

 

 

 

Light To My Path Book Distribution

Sydney Mines, N.S. CANADA B1V1Y5


የጸጋው ፍሬያማነት

የቅጂ መብት ฉ 2017 በኤፍ. ዋይኑ ሌዎድ

መብት ሁሉ የተጠበቀ ነው፡፡ከጸሐፊው የጽሑፍ ፈቃድ ውጪ፤የትኛውም የዚህ መጽሐፍ አካል በማንኛውም መልክ ወይም መንገድ ሊሰራጭ ወይም ሊተላለፍ አይችልም።

“በዚሀ መጸሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የተወሰዱት ESVฎ Bible (The Holy Bible, English Standard Versionฎ), copyright ฉ 2001 by Crossway, a publishing ministry of Good News Publishers. ነው፡፡ የተፈቀደ፡፡ መብት ሁሉ የተጠበቀ ነው፡፡”

ልዩ ምስጋና በእርማት ለረዳችኝ፤

ለዲያን ማክ ሎይድ

 


ማውጫ

መቅድም... 5

ምዕራፍ 1-  አሳቹ እና የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች   7

ምዕራፍ  2-  ሃገር እና ሕዝብ የሌለው ሰው... 19

ምዕራፍ  3-  በቀለኛው ብርቱ ሰው እና የእስራኤል ጠላቶች ሽንፈት   29

ምዕራፍ  4-  በሃገር ላይ ተጽዕኖ ያመጣው ታጋዩ አባት   38

ምዕራፍ  5-  የእግዚአብሔርን ጸጋ የሚለማመደው እረኛ   47

ምዕራፍ  6- በነብያት ድካም የሚገለጠው የእግዚኢብሔር ኃይል   59

ምዕራፍ 7 -  የባዕድ ነገስታት እና የእግዚአብሔር ዓላማ    68

ምዕራፍ 8 -  ኢየሱስ የመረጣቸው ሰዎች.. 79

ምዕራፍ 9 -  ዓለማዊ ስኬት እና ታማኝነት.. 87

ምዕራፍ10 - ምስጋናውን መውሰድ.. 97

ምዕራፍ11 - ዓለማዊ ስኬት እና ቅድሚያ የሚሰጣቸው መንፈሳዊ ጉዳዩች   104

ምዕራፍ 12 -  በድካም ውስጥ ያለ ፍሬያማነት.. 112

ምዕራፍ 13 -  የማጠቃለያ ሐሳቦች.. 119

መቅድም

በዘመናችን በአገልግሎት የበለጠ ውጤታማ ስለመሆን የሚያስተምሩ ብዙ ስልጠኛዎች እና መጻሕፍት አሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶች እና ስልጠናዎች እንዴት የተሻለ ሰባኪ መሆን እንደምትችሉ መመሪያ ይሰጣሉ። አብያተ ክርስቲያናትን እንዴት መትከል እና ማሳደግ እንዳለብን የሚያሳዩ ጉባኤዎች አሉ። እነዚህ ክስተቶች በጣም ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። በግሌ እግዚአብሔር እነዚህን አጋጣሚዎች ተጠቅሞ አገልግሎቴን ለመቅረፅ ረድቶኛል። ለአንዳንድ መንፈሳዊ እድገቴ የሚሆኑ ጠቃሚ ነገሮችን ለማግኘት እንደዚህ ዓይነት ስልጠኛዎች ማግኘት አስፈላጊ ነው።

ይህ ዓይነቱ ሥልጠና ጠቃሚ ቢሆንም፣የበለጠ መረዳት የሚያስፈልገን መንፈሳዊ ውጤታማነት እና ፍሬያማነት የተመሠረተው በትምህርታችን ወይም በምንጠቀማቸው ዘዴዎች ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ መሆኑ ነው። ለመንግሥቱ የምንጠቀመው የሰለጠንን ስለሆን ሳይሆን እግዚአብሔር በጸጋው በእኛ ለመጠቀም በመምረጡ ምክንያት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስን ሳጠና፤ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር በሚጠቀምባቸው ሰዎች እደነቃለሁ። ምናልባት መደበኛ ሥልጠና ያልነበረውን ሰው እግዚአብሔር በኃይል ሙሉ በሙሉ ሲጠቀምበት ስታዩ በአገልግሎት ውጤታማ ለመሆን ዓመታትን በሥልጠና ያሳለፋችሁት ጊዜ ወደ አዕምሯችሁ ይመጣ ይሆናል። ምናልባት በቅድስና እና በቅንነት ለመኖር የተቻላችሁን ሁሉ አድርጋችሁ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ክርስቲያናዊ የሆነ የሕይወት ምስክርነት የሌለውን ሰው ለምን ይጠቀማል ብላችሁ ታስቡ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር የሰለጠኑ እና በጥሩ የአኗኗር ዘይቤ የሚመላላሱ ሰዎችን በመጠቀም ብቻ የተወሰነ አይደለም። እሱ ብዙውን ጊዜ አጠያያቂ የሆነ የኋላ ታሪክ እና ታማኝነት ያላቸው ወንዶችን እና ሴቶችን ተጠቅሟል። ፍሬያማነት በእኔ ማንነት ወይም ተሰጥኦ የሚመጣ ሳይሆን የእግዚአብሔር ድንቅ ጸጋ ውጤት መሆኑን ወደ መረዳት እየመጣሁ ነው።

የዚህ ጥናት ትኩረት እግዚአብሔር የሚጠቀምባቸውን ዓይነት ሰዎች መርምሮ ማወቅ ነው። ከትምህርት ወይም መልካም የአኗኗር ዘይቤ አስፈላጊነት ጋር በተያያዘ የማነሳው ምንም ጥያቄ የለኝም። ሆኖም እኔ ማሳየት የምፈልገው በአገልግሎት ውስጥ የሚመጣ ውጤታማነት የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ብቻ ነው። የአገልግሎታችን ስኬት እና ፍሬያማነት የመጣው በመልካም ትምህርታችን፣በክህሎታችን ወይም መልካም አኗኗራችን ምክንያት የመጣ በማድረግ ለእግዚአብሔር ክብርን በመስጠት ፈንታ ምስጋናውን ለራሳችን እንወስድ ይሆን?

ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ፣በአገልግሎት ውስጥ የሚመጣ ውጤታማነት ከእኔ ጥረት ይልቅ በእግዚአብሔር ላይ የተደገፈ መሆኑን እረዳለሁ። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ትምህርቴ እና ልምዴ እንቅፋት ስለሆኑብኝ እግዚአብሔርን መታመን እና መፈለግን አልቻልኩም ነበር። ከእኔ ጋር ይህንን ጥናት ስትጀምሩ ለፍሬያማ አገልግሎት የእግዚአብሔር ጸጋ እንደሚስፈልጋችሁ እንደሚያስታውሳችሁ አምናለሁ።

 

ኤፍ. ዋይኒ ማክ ሌዎድ

 


ምዕራፍ 1- አሳቹ እና የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል

ይህንን ጥናት ስንጀምር፤ግባችን በወንዶች እና ሴቶች ልጆች በጉድለቶቻቸው እና ድካማቸው ዓላማዎቹን የሚገለጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ ማየት ነው።እግዚአብሔር እንዲጠቀምብን ፍጹም መሆን ስለማያስፈልገን ምን ያህል አመስጋኞች ነን።

ጥናታችንን ያዕቆብ ከተባለው ሰው እንጀምር። ያዕቆብ የታላቁ የአይሁድ አባት የሆነው ይስሐቅ ልጅ ነበር። የይስሐቅ ሚስት ርብቃ ልጅ መውለድ አትችልም ነበር። እግዚአብሔር የይስሐቅን ጸሎት ሰምቶ ማህፀኗን ከፈተላት። (ዘፍጥረት 25:21 ተመልከቱ) ርብቃም ጸነሰች ከዚያም መንታ ልጆችን ያዕቆብንና ወንድሙን ኤሳውን ወለደች።

በዚህ ጸንሰ-ሀሳብ ውስጥ ጉልህ የሆነው ስለ እነዚህ መንትዮች የተነገረው ትንቢት ነበር። በእርግዝናዋ ወቅት ርብቃ የሆነ ችግር እንዳለ ይሰማት ነበር። መንትዮቹ “በሆድዋ ውስጥ ይገፋፉ ነበር፤” (ዘፍጥረት 2522) ይህ ርብቃን ስላስጨነቃት ጌታን ስለዚህ ጉዳይ ጠየቀች፡

23 እግዚአብሔርም አላት፦ ሁለት ወገኖች በማኅፀንሽ ናቸው፥ ሁለቱም ሕዝብ ከሆድሽ ይከፈላሉ፤ሕዝብም ከሕዝብ ይበረታል፤ታላቁም ለታናሹ ይገዛል። ዘፍጥረት 25

እግዚአብሔር ለእነዚህ ሁለት ልጆች ዓላማ ነበረው። የሁለት የተለያየ ሕዝብ አባት ይሆናሉ። የእግዚአብሔር ዓላማ ግን ታናሹ ከወንድሙ የበለጠ ጠንካራ እንዲሆን እና ታላቁም ታናሹን እንዲያገለግል ነበር።

የመውለጃው ጊዜ ሲደርስ የበኩር ልጁ ኤሳው ሲባል ታናሹም ያዕቆብ ተብሎ ተጠራ። ልብ ሊባል የሚገባው ነገር፣ኤሳው ሲወለድ፣ታናሽ ወንድሙ ያዕቆብ ተረከዙን ይዞ ነበር። ወላጆቹ ይህንን ክስተት አስተውለው ድርጊቱን የሚወክል ስም ሰጡት። አዳም ክላርክ ለያዕቆብ ስለተሰጠው ስም እንዲህ ይላል፡

ስሙ ያዕቆብ ብሎ ተጠራ–ያም ከአዕካብ የተወሰደ ነው፤ትርጓሜውም፤ተንኮል፤ማታለል፤ማፈናቀል .. ማለት ነው፤የአንድን ሰው ተረከዝ በመያዝ መገልበጥ ማለት ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ይህ ስም ለያዕቆብ ተሰጠ፤ምክንያቱም የወንድሙን ተረከዝ ይዞ ነበርና፤ያም የወንድሙን ኤሳውን ስፍራ ስለመያዙ እና ብኩርናውን በማታለል ስለመውሰዱ ምሳሌ ነበር፡፡ (Commentary on the Bible by Adam Clarke (CLARKE) Electronic edition copyright ฉ 2015 by Laridian, Inc., Marion Iowa. All rights reserved. “Commentary on the Bible by Adam Clarke.” Marion, IA: Laridian, Inc., 2015)

ልጆቹ እያደጉ ሲሄዱ ይህ የያዕቆብ የማታለል ባህሪ በግልጽ ይታይ ነበር። ዘፍጥረት 25 ያዕቆብ በቤት ወጥ እየሰራ የነበረበትን ክስተት ይገልጻል (ዘፍጥረት 25:29) በሌላ በኩል ኤሳው ሜዳ ላይ አደን ለማደን ወጥቶ ነበር። ኤሳው ወደ ቤቱ ሲመለስ በጣም ተርቦ ነበርና ወንድሙን እየሰራው ከነበረው ወጥ እንዲሰጠው ጠየቀው።

የወንድሙን ረሀብ በመጠቀም ያዕቆብ ለኤሳው ብኩርናውን ሲሸጥለት ብቻ ከሰራው ወጥ እንደሚሰጠው ነገረው። ኤሳው ከሁለቱ ወንዶች ልጆች በኩር በመሆኑ ርስቱ ከያዕቆብ ይበልጥ ነበር። ያዕቆብ በዚህ ቅር ተሰኝቷል። ኤሳው የሚበላ ነገር ካላገኘ የሚሞት መስሎ ተሰማው፤ስለሆነም ለያዕቆብ በወጡ ምትክ ብኩርናውን እንደሚሰጠው ማለለት። ኤሳውም ይህን መሐላ በመማሉ ምክንያት ታናሹ ለታላቁ ይገዛል የሚለውን ለእናቱ ለርብቃ የተነገረውን የትንቢት ቃል በመፈጸም ለታናሽ ወንድሙ መብቱን በሕጋዊ መንገድ አሳልፎ ሰጠው። ይህ መብት ግን በተንኮል የተወሰደ ነበር።

የያዕቆብ የማጭበርበር እና የማታለል ባሕርይ ወንድሙን በችግር ጊዜ በያዘበት መንገድ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በአባቱ የእርጅና ዘመን ባደረገው ነገርም ታይቷል። ዘፍጥረት 27 ያዕቆብ የአባቱን የአይን ዕይታ ችግር እንዴት እንደተጠቀመበት ይተርካል። ይስሐቅ እያረጀ መሆኑን በማወቁ የበኩር ልጁን በልዩ በረከት ሊባርከው ፈልጎ ነበር። ይህ ቀላል ጉዳይ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል። የበኩር ልጁ በረከት በጣም አስፈላጊ ክስተት ነበር። ይህ በረከት ከአባት ብቻ የሚሆን ሳይሆን በአባቱ በኩል የመጣ የእግዚአብሔር በረከት ነበር። የኤሳው የወደፊት ዕጣ ፈንታ በዚህ በረከት ውስጥ ከአባቱ ቃላት ጋር በጥልቀት ተቆራኝቷል።

ይስሐቅ አብረው እንዲበሉ እና ይህን በረከት እንደ አባት እና ልጅ አድርገው እንዲያትሙት ልጁን ኤሳውን ወጥቶ ጥቂት ሥጋ አድኖ እንዲያመጣለት ነገረው። ይስሐቅ ልጁን ኤሳውን ሊባርከው መሆኑን ሲሰሙ ርብቃ እና ያዕቆብ ኤሳውን ለማታለል እና በረከቱን ለመውሰድ ዕቅድ አወጡ። ርብቃ ከመንጋው ውስጥ ለባሏ የተወሰነ ሥጋ አዘጋጀች። ያዕቆብ እንደ ወንድሙ ጸጉራም ሆኖ እንዲታይ የኤሳውን ልብስ ለብሶ ሰውነቱን በፍየል ቆዳ ሸፈነ። ያዕቆብም ስጋውን ወደ አባቱ አምጥቶ የወንድሙን በረከት ተቀበለ። ይስሐቅ ዓይኑ ታውሮ ስለነበር ለታናሹ ልጅ በረከቱን መስጠቱን አላወቀም ነበር። በዚህ መንገድ ያዕቆብ የኤሳውን በረከት ሰረቀበት።

ያዕቆብ ለወንድሙ እና እንደ በኩር ልጅ ላለው ቦታ አክብሮት ባለማሳየቱ እዚህ ጋር ቅር ተሰኝተናል። በዚህ መንገድ በማታለል አባቱን በእርጅና ዘመኑ ለማዋረድ ፈቃደኛ መሆኑን እንመለከታለን።

በድርጊቱ ምክንያት ያዕቆብ ከቤት ለመውጣት ተገደደ። ኤሳው በእሱ ላይ በጣም ስለተቆጣ አባቱ በሞተበት ቅጽበት ያዕቆብን ለመግደል ማለ። ኤሳው፣ቢያንስ ለአባቱ በቂ አክብሮት ነበረው፣በሕይወት እያለ ወንድሙን በመግደል ልቡን ለማሳዘን አልፈለገም። ያዕቆብ ከወንድሙ ቁጣ ለማምለጥ በእናቱ በኩል አጎቱ ወደሚኖርበት ወደ ካራን ምድር ሸሸ።

ያዕቆብ ወደ ካራን ምድር በተጓዘበት ጊዜ፤እግዚአብሔር በሕልም ለያዕቆብ ተናገረው፡

13…እነሆም፥ እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር፥ እንዲህም አለ፦ የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ፤14 ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል፤ እስከ ምዕራብና እስከ ምሥራቅ እስከ ሰሜንና እስከ ደቡብ ትስፋፋለህ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በአንተ በዘርህም ይባረካሉ። 15 እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና። (ዘፍጥረት 28)

እነዚህ ቃላት በአውድ ውስጥ እንግዳ ናቸው። ያዕቆብ ከተናደደው ወንድሙ እየሸሸ ነው። ይህን እያደረገ ያለው እሱን በማታለሉ እና በረከቱን ለወሰደበት ነው። ሆኖም፣ ሕይወቱን ለማዳን ሲሸሽ፣ የበረከቱን ተስፋ ከሰጠው ጌታ እግዚአብሔር ጋር ተገናኘ። በዚህ አታላይ ሰው አማካኝነት የምድር አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉና። እግዚአብሔር ያዕቆብን የተናገረውን ሁሉ እስኪፈጽምለት ድረስ አይተወውም።

ገና ከመጀመሪያው ያዕቆብ የእግዚአብሔርን በረከት እንደሚቀበል ጌታ ለርብቃ አሳይቷት ነበር። ያዕቆብ ከወለደቻቸው ሁለት ልጆች የበለጠ ጠንካራ ይሆናል። እንደዚያ ስንል ያዕቆብ ከወንድሙ የተሻለ ነው ማለት ነውን? የእነዚህ ሁለት ወንዶች ልጆች ታሪክ ይህ እንዳልሆነ እንድናምን ያደርገናል። ያዕቆብ በዙሪያው ያሉትን ሰዎች ማክበር ያልቻለ አታላይ ነበር። እሱ ለራሱ ጥቅም ሲል ሰዎችን ሆን ብሎ ይጠቀማል። እንግዲህ እግዚአብሔር በዚያ ቀን በሕልም የባረከው ሰው ይህ ነው። ፍጽምና የጎደለው ሰው ነበር። የእግዚአብሔር በረከት ያዕቆብ ብቁ ከመሆኑ ጋር ምንም ግንኙነት አልነበረውም። ይህ የእግዚአብሔር ምሕረት እና ጸጋ ድርጊት ነበር።

ያዕቆብ በካራን ምድር ሁለት ሚስቶችን አገባ። እግዚአብሔር ልያ እና ራሔል ከተባሉት ሚስቶቹ አሥራ ሁለት ልጆችን ሰጠው። እነዚህ ልጆች የአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች አባት ናቸው። ታላቁ የእግዚአብሔር ዓላማ በአታላዩ በያዕቆብ በኩል ተፈጸመ።

የያዕቆብ ኃጢአተኛ ባህሪ ምንም ዋጋ እንዳላስከፈለው እንዳናስብ፣ ከያዕቆብ ሕይወት ጋር የሚዛመዱ ጥቂት ተጨማሪ ዝርዝሮችን ላስታውሳችሁ።የያዕቆብ አታላይነት የራሱ ውጤቶች ነበሩት።

በመጀመሪያ፣ያዕቆብ አብዛኛውን የሕይወቱን ክፍል የወንድሙን በቀል በመፍራት ይኖር ነበር። እግዚአብሔር ወደ ከነዓን ምድር በጠራው ጊዜ ያዕቆብ የተመለሰው በልቡ ታላቅ ፍርሃት ይዞ ነበር። ዘፍጥረት 32 የዚያን የፍርሃት መጠን ይገልጻል። በዚህ ጉዳይ ላይ ከጌታ መልአክ ጋር ይታገል ነበር። ከወንድሙ ጋር የነበረው ይህ የተበላሸ ግንኙነት በጉልምስና ህይወቱ የተሸከመው ሸክም ሆኖ ቆይቷል።

ሁለተኛ፣ያዕቆብ ከአጎቱ ከላባ ጋር ይኖር ነበር። ላባ ያዕቆብ ለሰባት ዓመታት የሚያገለግለው ከሆነ ልጁን ራሔልን እንደሚድርለት ቃል ገብቶለት ነበር። ሆኖም በሠርጉ ምሽት ላባ በምትኩ ታላቋን ልያን ሰጠው። ነገሩ በታወቀ ጊዜ ላባ ያዕቆብ ለራሔል ሌላ ሰባት ዓመት እንዲሠራለት ጠየቀው። አታላዩ ራሱ ተታለለ። ያዕቆብ ከአማቱ ላባ ጋር በነበረው ግንኙነት ራሱ ብዙ ጊዜ ተታሏል። በዘፍጥረት 31 ላይ ለሚስቶቹ የነገራቸውን አዳምጡ፡

6 እኔ ባለኝ ጕልበቴ ሁሉ አባታችሁን እንዳገለገልሁ ታውቃላችሁ። 7 አባታችሁ ግን አታለለኝ፥ ደመወዜንም አሥር ጊዜ ለወጠ፤ እግዚአብሔር ግን ክፉን ያደርግብኝ ዘንድ አልፈቀደለትም። (ዘፍጥረት 31)

አታላይ የሆነው ያዕቆብ ዘወትር በእርሱ የሚጠቀምበት አማት ባለው በቤተሰብ ውስጥ ራሱን አገኘው። ይህ በጣም የተበላሸ የቤተሰብ ግንኙነትን አስከትሏል።

ሦስተኛ የያዕቆብ ሚስቶች ሁልጊዜ እርስ በእርስ በእርሳቸው ይፎካከሩ ነበር። ራሔል እና ሊያ ሁለቱም ያዕቆብን ትኩረት ለመሳብ ይታገሉ ነበር። ራሔል ልጅ መውለድ ስላልቻለች በምሬት ታጉረመርም ነበር። ሊያ ሁልጊዜ የማትወደድ ሚስት እንደሆነች ይሰማት ነበር። የያዕቆብ ሚስቶቹ እርስ በእርስ በነበራቸው ሙግት ምክንያት በመሃል ተይዞ ነበር። ራሔል በአገልጋይዋ ባላ በኩል እግዚአብሔር ልጅ ሲሰጣት የተናገረችውን አድምጡ፡

8 ራሔልም፦ ብርቱ ትግልን ከእኅቴ ጋር ታገልሁ፥ አሸነፍሁም አለች፤ ስሙንም ንፍታሌም ብላ ጠራችው። (ዘፍጥረት 30)

የያዕቆብ ቤተሰብ ችግሮች በሚስቶቻቸው የሚያበቃ አልነበረም። ዘፍጥረት 34 ሴት ልጁ ዲና በሚኖሩባት ምድር ከአንዳንድ ወጣት ልጃገረዶች ጋር እንደወጣች እና ሴኬም ከሚባል ወጣት ጋር እንዴት እንደተገናኘች ይተርካል። ሴኬም ዲናን በማታለል ደፈራት።

የያዕቆብ ልጆች በእህታቸው ላይ የሆነውን ነገር በሰሙ ጊዜ በጣም ተቆጡ። ሴኬም እና አባቱ ስለዚያ ክስተት ያዕቆብን ለማግኘት ወደ እርሱ መጡ። የሴኬም አባት ሔሞር ያዕቆብን የሙሽራ ዋጋ እንዲወስንለት እና ልጁ ሴኬም ዲናን ያገባ ዘንድ ጠየቀው።የያዕቆብ ልጆች ለዚህ ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ አዳምጡ፡

13 የያዕቆብም ልጆች ለሴኬምና ለአባቱ ለኤሞር በተንኰል መለሱ፥ እኅታቸውን ዲናን አርክሶአታልና፤ 14 እንዲህም አሉአቸው፦ እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ለመስጠት ይህንን ነገር እናደርግ ዘንድ አይቻለንም፤ ይህ ነውር ይሆንብናልና።15 እንደ እኛ ሆናችሁ ወንዶቻችሁን ሁሉ ብትገርዙ በዚህ ብቻ እሺ እንላችኋለን፤ (ዘፍጥረት 34)

በጉዳዩ ተስማምተው ሴኬምና ሔሞር ወደ ቤታቸው ሄደው የከተማቸውን ወንዶች ሁሉ እንዲገረዙ አደረጉ። ነገር ግን አስተውሉ፣ ዘፍጥረት 34:13 የያዕቆብ ልጆች በጥያቄአቸው አታላዮች እንደነበሩ ይነግረናል። ግርዛቱ ከተፈጸመ ከሦስት ቀናት በኋላ ስምዖንና ሌዊ ሰይፋቸውን ይዘው ሰዎቹ ገና ከቁስላቸው ሳያገግሙ ሁሉንም ሲገድሉ ተንኮል ተገለጠ።

የያዕቆብ አታላይነት ወደ ልጆቹ ተላልፎ ነበር። በዚህ ሁኔታ ያዕቆብ ለዚህ የሚከፍለው ከባድ ዋጋ ነበር። በዚያ ቀን ለልጆቹ ሲናገር እንዲህ አለ፡

30 ያዕቆብም ሌዊንና ስሞዖንን እንዲህ አለ፦ በዚች አገር በሚኖሩ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ሰዎች የተጠላሁ ታደርጉኝ ዘንድ እኔን አስጨነቃችሁኝ፤ እኔ በቍጥር ጥቂት ነኝ፤ እነርሱ በእኔ ላይ ይሰበሰቡና ይመቱኛል፤ እኔም ከወገኔ ጋር እጠፋለሁ። (ዘፍጥረት 34)

በዘፍጥረት 35:22 ላይ የያዕቆብ የበኩር ልጅ ሮቤል ከቁባቱ ጋር በመተኛት አባቱን እንዴት እንዳዋረደ እናነባለን። ራሱ አባቱን በእርጅና ዕድሜው ያላከበረ ሰው አሁን ይህንን ህመም እና ውርደት በገዛ ልጁ በኩል ደረሰበት።

ያዕቆብ፣ዘወትር ከሚያታልለው ከላባ ጋር ባለው ግንኙነት ችግር ላይ ነበር። እንዲሁም ሁልጊዜ ከሚጣሉ እና አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ለመጠቀም ሁልጊዜ እየሞከሩ ካሉ ሁለት ሚስቶች ጋር ይኖር ነበር። ልጆቹ በውስጣቸው ይህ የማታለል ተፈጥሮ ነበራቸው፤ስለሆነም በአንድ ከተማ ውስጥ ላሉት ወንዶች ግድያ ተጠያቂዎች ነበሩ። ይህ ማታለል ከአከባቢው ህዝቦች ጋር የነበረውን ግንኙነት አበላሽቷል። የበኩር ልጁ የሆነው ሮቤል ከቁባቱ ጋር በመተኛት አዋርዶታል።

እግዚአብሔር ሊባርከው የወሰነው ሃገር አባት ለመሆን የምትመርጡት ሰው ይህ ይሆን? ቤተሰቦቹ ችግር ውስጥ ያሉ ይመስላል። የግል ሕይወቱ መሆን ያለበት ቦታ አልነበረም። በማህበረሰቡ ውስጥ የሰጠው ምስክርነት አጠያያቂ ነበር።  ሆኖም በዚህ አታላይ ሰው አማካኝነት አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ተወለዱ።

ከሴኬም እና ዲና ክስተት በኋላ እግዚአብሔር ያዕቆብን አከባቢውን ለቆ ወደ ቤቴል እንዲሄድ ተናገረው (ዘፍጥረት 35:1) ዘፍጥረት 35:5 ስለዚያ ጉዞ ምን እንደሚነግረን አስተውሉ፡

5 ተነሥተውም ሄዱ፤የእግዚአብሔርም ፍርሃት በዙሪያቸው ባሉት ከተሞች ሁሉ ወደቀ፥የያዕቆብንም ልጆች ለማሳደድ አልተከተሉአቸውም። (ዘፍጥረት 35)

የትኛውም ሰው ሊያጠቃቸው እንዳይደፍር የያዕቆብ ልጆች በሚጓዙበት ጊዜ የእግዚአብሔር ጸጋ ይጠበቃቸው ነበር።

እግዚአብሔር የያዕቆብን ስም ወደ እስራኤል ለወጠው፣ ትርጓሜውም “ከእግዚአብሔር ጋር የሚታገል” ማለት ነው። ነገር ግን ከዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ለታገለው ሰው አንድ የተስፋ ቃል ተሰጠው።

10 እግዚአብሔርም፦ ስምህ ያዕቆብ ነው፤ ከእንግዲህም ወዲህ ስምህ ያዕቆብ ተብሎ አይጠራ፥ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ አለ፤ ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው። 11 እግዚአብሔርም አለው፦ ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ፤ ብዛ፥ ተባዛም፤ ሕዝብና የአሕዛብ ማኅበር ከአንተ ይሆናል፥ ነገሥታትም ከጕልበትህ ይወጣሉ። 12 ለአብርሃምና ለይስሐቅም የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ ምድሪቱን እሰጣለሁ። (ዘፍጥረት 35)

እግዚአብሔር ለያዕቆብ ያቀረበው ጥሪ ፍሬያማ እና መብዛት ነበር። የአባቶቹ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ምድርን እና ዘርን ይሰጠዋል። በዚያ ዘር በኩል ምድር ሁሉ ይባረካል።

የያዕቆብ ምስክርነት ከፍጹምነት የራቀ ነው። በግለሰብ ደረጃ በሕይወቱ ውስጥ ብዙ ጉዳዮች ነበሩት። ቤተሰቡ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነበር። በልጆቹ ድርጊት ምክንያት በማህበረሰቡ ዘንድ የነበረው ምስክርነት ተበላሽቷል። እግዚአብሔር ይህን ሰው “ፍሬያማ እንዲሆን እና እንዲበዛ” ጠራው። እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ጠብቆት በእርሱ ለመጠቀም መረጠ። ያዕቆብ ሕይወቱን ወደ ኋላ ሲመለከት ሁሉንም ድክመቶቹን እንደሚያውቅ እርግጠኛ ነኝ። በእነዚያ ድክመቶች በግል እና በቤተሰብ ሕይወቱ እንዲሁም በማኅበረሰቡ ውስጥ የነበረውን አሳዛኝ ውጤት ተመልክቷል። እንግዲህ በዚህ ሁሉ ነገሮች ውስጥ ቢያልፍም፣ ጌታ እሱን ለመባረክ እና ለመጠቀም የመረጠውን አስደናቂ የእግዚአብሔር ጸጋ ያውቅ ነበር።

 

ለምልከታ፡

•              ከርብቃና ከይስሐቅ ከተወለዱት መንትዮች ታናሽ ለሆነው ለያዕቆብ የእግዚአብሔር ዓላማ ምን ነበር?

•              ያዕቆብ የታላቅ ወንድሙን የኤሳውን በረከት እና ብኩርና እንዴት ወሰደ?

•              ያዕቆብ በአታላይነቱ ምክንያት ከቤት ለመውጣት ተገዶ ነበር። ወደ ካራን ምድር ሲሄድ ጌታ እንዴት ተገናኘው? እግዚአብሔር ለያዕቆብ የገባው ቃል ምን ነበር?

•              በያዕቆብ ቤተሰብ ውስጥ ምን እየተከናወነ እንደነበር ግለጹ። በዚህ መልስ ውስጥ ሚስቶቹን እና ልጆቹን አስቧቸው።

•              የያዕቆብ ልጆች ሴኬምንና የከተማዋን ሰዎች ከገደሉ በኋላ እግዚአብሔር መገኘቱን ለእነርሱ እንዴት ገለጸ? ዘፍጥረት 35:5 ተመልከቱ።

•              ያዕቆብን ለበረከትና ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ያበቃው ምን ነበር? እንግዲህ ይህ ሰው የእግዚአብሔር በረከት እና የተስፋ ቃል መጠቀሚያ መሣሪያ እንዲሆን ትመርጡታላችሁን?

•              የያዕቆብ አታላይነት በግል ሕይወቱ ያስከተላቸው ውጤቶች ምን ነበሩ?

 

ለጸሎት፡

•              ከእግዚአብሔር ቃል ትምህርት እና ለሕይወታችሁ ካለው ዓላማ ጋር የማይጣጣም ማንኛውንም ነገር እንዲገልጥ ጌታን ጠይቁ።

•              የግል ጉድለቶች እና ድክመቶች ቢኖርባችሁም እርሱ ምህርት ስላደረገላችሁ ጌታን አመሰግኑ።

•              ቤተሰባችሁን ወደ እሱ ለማሳደግ ባላችሁ መሻት ጌታ ጥበብን እንዲሰጣችሁ ጠይቁ።

•              በኃጢአታችሁ ምክንያት የመጣባችሁን ውጤቶች መጋፈጥ ነበረባችሁን? እርሱን በሚያከብር መንገድ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በአግባቡ ለመጓዝ ጌታ ብርታትን እንዲሰጣችሁ ጠይቁ።

•              ከእርሱ ክብር ስንጎድል እኛን ስለማይተወን ጌታን አመስግኑት።

•              ምንም እንኳን ድካም ቢኖርበትም የአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች አባት ይሆን ዘንድ ያዕቆብን ስለተጠቀመበት መንገድ ጌታን አመስግኑት።


 

ምዕራፍ 2 - ሃገር እና ሕዝብ የሌለው ሰው

የሙሴ ሕይወት የጀመረው በግብፅ ምድር ነበር። አባቱ ሌዋዊ ነበር (ዘጸአት 21) ስለዚህ እርሱ የተወለደው እግዚአብሔር የክህነቱ ወኪል እንዲሆኑ በመርጠው ነገድ ውስጥ ነበር። የእስራኤል ሕዝብ የራሳቸው መሬት አልነበራቸውም። በመሠረቱ፣ ሙሴ በተወለደ ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ በግብጻውያን ዘንድ እንደ ባሪያ ሆነው ሲኖሩ እና በደል ይደርስባቸው እና ይሰቃዩ ነበር። ይህ በደል በጣም ጨካኔ የሞላበት ከመሆኑ የተነሳ ፈርዖን ከእስራኤል ሴት የተወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ ወደ አባይ ወንዝ እንዲጣል ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። (ዘፀአት 122)

የሙሴ እናት ከግብፃውያን ባለሥልጣናት እሱን ለመደበቅ የተቻላትን ሁሉ ሞክራ ነበር፣ደግሞም ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ፥ የደንገል ሣጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም አኖረችበት፥ በአባይ ወንዝም ዳር ባለ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው የፈርዖንም ልጅ ልትታጠብ ወደ ወንዝ ወረደች፤ ደንገጥሮችዋም በወንዝ ዳር ይሄዱ ነበር፤ ሣጥኑንም በቄጠማ ውስጥ አየች፥ ደንገጥርዋንም ልካ አስመጣችው።በከፈተችውም ጊዜ ሕፃኑን አየች፥ እነሆም ሕፃኑ ያለቅስ ነበር፤ አዘነችለትም ወስዳም እንደራሷ ልጅ አድርጋ ለማሳደግ ወሰነች (ዘጸ 23-11) ሙሴ እንደ ግብጻዊ ከወገኖቹ ተለይቶ አደገ። ይህ ከገዛ ወገኖቹ መሰደዱ ደስ የሚያሰኝ ባይሆንም ሙሴን ያስጨንቀው ነበር።

ዘጸአት 21112 ሙሴ ባደገ ጊዜ የራሱን ህዝብ ለማየት እንዴት እንደ ወጣ ይተርካል። በዕለቱ ያየው ነገር ግን አበሳጨው። አንድ ግብፃዊ አንድ እስራኤላዊን ሲደበድብ ተመለከተ። ዘጸአት 212 በምላሹ ያደረገውን ይናገራል:

12 ወዲህና ወዲያም ተመለከተ፥ ማንንም አላየም፥ ግብፃዊውንም ገደለ፥ በአሸዋም ውስጥ ሸሸገው።  (ዘጸአት 2)

ሙሴ ይህን ግብፃዊ የገደለው እስራኤላዊውን ባሪያ ስለደበደበ ነው። እሱ ያደረገው ስህተት መሆኑን ያውቅ ነበር። ምንባቡ እንደሚነግረን “ወዲህና ወዲያም ተመለከተ፥ ማንንም አላየም፥ ግብፃዊውንም ገደለ፥ በአሸዋም ውስጥ ሸሸገው።” ይላል። በግልጽ እንደሚታየው ሙሴ ለመያዝ አልፈለገም ነበር። የሐዋርያት ሥራ 7:23-25 ሙሴ ይህን ግብፃዊ ለመግደል ለምን እንደፈለገ ይነግረናል።

23 ነገር ግን አርባ ዓመት ሲሞላው ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ይጐበኝ ዘንድ በልቡ አሰበ። 24 አንዱም ሲበደል አይቶ ረዳው፥ የግብፅን ሰውም መትቶ ለተገፋው ተበቀለ። 25 ወንድሞቹም እግዚአብሔር በእጁ መዳንን እንዲሰጣቸው የሚያስተውሉ ይመስለው ነበር፥ እነርሱ ግን አላስተዋሉም።

ሙሴ ለሕዝቡ ሸክም ስለነበርው ሊረዳቸው እንደሚችል ያምን ነበር። በፈርዖን ሴት ልጅ ያደገ እንዲሁም በሃገሩ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ እና ስልጣን ያለው ሰው ነበር። በእስራኤል ያሉትን ወንድሞቹንና እህቶቹን ሊረዳቸው እንደሚችልና እሱ ከጎናቸው መሆኑን ለማሳየት ፍላጎት ነበረው።

ይህ የሙሴ ድርጊት የሚያሳየን በግብፅ ምቾት ውስጥ ቢያድግም ልቡ ግን በዚያ እንዳልነበረ ነው። እሱ የእስራኤል ስለሆነ ወደ ወገኖቹ ተመልሶ በችግራቸው ጊዜ ሊረዳቸው ይፈልግ ነበር። ከውጭ የሚታየው የስደት ኑሮው ምቹ ቢሆንም ዳሩ ግን በውስጣዊው ስሜቱ እና መንፈሱ ሙሴ ደስተኛ አልነበረም። ሙሴ ራሱን ከህዝቡ እንደተለየ ስደተኛ ይመለከት ነበር።

በሌላ አጋጣሚ ወደ ወገኖቹ ሲመለስ፤ሙሴ ሁለት እስራኤላውያን ሲጣሉ ተመለከተ። እነዚህን ሰዎች ለምን እርስ በርሳቸው እንደሚጣሉ ጠየቃቸው። ሆኖም ምላሻቸው ለሙሴ በጣም አስደንጋጭ ነበር፡

14 ያም፦ በእኛ ላይ አንተን አለቃ ወይስ ዳኛ ማን አደረገህ? ወይስ ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትሻለህን? አለው። ሙሴም፦ በእውነት ይህ ነገር ታውቆአል ብሎ ፈራ። (ዘጸአት 2)

በዚያ ቀን እነዚያ ቃላት በሁለት ምክንያቶች የሙሴን ነፍስ በጥልቀት ወግተውት መሆን አለባቸው። በመጀመሪያ፣ የእስራኤላዊው ቃል ሙሴ ግብፃዊውን እንደገደለ እና በአሸዋ ውስጥ እንደሸሸገው ማወቁን ይገልጣል። እስራኤላውያን ስለዚህ ጉዳይ ካውቁ ብዙም ሳይቆይ የግብፅ ባለሥልጣናትም ያውቁታልና። ሙሴ በነፍስ ግድያ ጥፋተኛ ነበር ስለሆነም ቢያዝ የሚመጣበትን መዘዝ ይፈራ ነበር።

በእኛ ላይ አለቃ እና ዳኛ ማን አደረገህ? የሚለው የዚህ ሰው ቃላት በጣም ጎጂ የሆነበት ሁለተኛው ምክንያት የእስራኤል ሕዝብ ልብ ለእርሱ ያለውን ሃሳብ ስለገለጡ ነው። እስራኤል ሙሴን እንደ እንደ አለቃቸው እና ተከላካይ አደርገው አልተቀበሉትም። ስለሆነም ከእሱ ጋር ምንም ለማድረግ አልፈለጉም። በእነርሱ እይታ፤እርሱ የእነርሱ አባል አይደለም። ብዙ ሰቆቃ እየደረሰባቸው ለፈርዖን እንዲሠሩ ሲገደዱ እርሱ በቅንጦት ይኖር ነበር። ሙሴ ያደገው ጠላቶቻቸው በሆኑ ሰዎች ነው፣እነሱም እንደ አንዱ አድርገው ይመለከቱት ነበር። ስላልተቀበሉትም የእርሱን እርዳታ አልፈለጉም።

ሙሴ በዚያ ቀን አገር የሌለው ሰው መሆኑን ሳይገነዘብ አልቀረም። እስራኤል እርሱን አልተቀበለውም። ፈርዖን ግብጻዊውን በመግደል ጥፋተኛ መሆኑን ሲያውቅ እሱን ለመግደል መፈለጉ አይቀርም። ሙሴ በስደት ከግብፅ ለመውጣት ተገደደ። ቀጣዮቹን አርባ ዓመታት ሕይወቱን በባዕድ የምድያም ምድር በጎችን በማገድ ያሳልፋል። ሙሴና ከምድያም ሚስቱ የመጀመሪያ ልጃቸውን በወለዱ ጊዜ ሙሴ ጌርሳም ብሎ ጠራው። ይህን ስም የሰጠበትን ምክንያት አስተውሉ፡

22 ወንድ ልጅም ወለደች፦ በሌላ ምድር መጻተኛ ነኝ ሲል ስሙን ጌርሳም ብሎ ጠራው። (ዘጸአት 2)

ሙሴ የስደት ሕይወቱን በጣም ያውቅ ነበር። እሱ አገር የሌለው እንዲሁም፣ እርሱን ከማይፈልገው እና ሊገድለው ከሚፈልገው ሃገር የተሰደደ ሰው ነበር። በምድያም ምድር እረኛ ሆኖ ለአርባ ዓመታት በስደት ኖረ።

ሙሴ ሰማንያ ዓመት እስኪሞላው እና ጌታ እግዚአብሔር እስከተገለጠለት ጊዜ ድረስ ከዚያ አልወጣም ነበር። ዘጸአት 3 ሙሴ በጎቹን እንደሚጠብቅ እና በበረሃ ውስጥ ቁጥቋጦ በእሳት የተቃጠለበትን ሁኔታ ይተርካል። እግዚአብሔር ከዚያ ቁጥቋጦ ውስጥ ሙሴን ተናገረው።

4 እግዚአብሔር እርሱ ይመለከት ዘንድ እንደ መጣ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ከቍጥቋጦው ውስጥ እርሱን ጠርቶ፦ ሙሴ፥ ሙሴ ሆይ አለ። 5 እርሱም፦ እነሆኝ አለ። ወደዚህ አትቅረብ፤ አንተ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ አለው። 6 ደግሞም፦ እኔ የአባትህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ አለው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ያይ ዘንድ ፈርቶአልና ፊቱን ሸፈነ። (ዘጸአት 3)

እግዚአብሔር ራሱን ለሙሴ እንዴት እንዳስተዋወቀ አስተውሉ። “እኔ የአባትህ አምላክ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅ አምላክ እና የያዕቆብ አምላክ ነኝ። እነዚህ ቃላት ሃገር አልባ ለሆነ እና የባለቤትነት ስሜት ለማይሰማው ስደተኛ ሰው ያላቸውን ትርጉም አቅልለን ማየት አንችልም። እግዚአብሔር በዚያ ቀን ሙሴ የአባቱ የአብርሃም አምላክ መሆኑን አስታወሰው። ይህም ሙሴን ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ለይቶታል። ለአርባ ዓመታት እንደ ግብፃዊ ሆኖ አደገ። ከዚያም በምድያም ምድር እረኛ ሆኖ ሌላ አርባ ዓመት ኖረ። እግዚአብሔር ግን ማንነቱንና ዓላማውን እያስተማረው ነው። እሱ የእስራኤላዊው የአብርሃም ልጅ መሆኑን ያስታውሰዋል።ይህ በእግዚአብሔር ፊት ማንነቱ ነበር።

ይህ ለሙሴ ልዩ ቀን መሆን አለበት። በእግዚአብሔር ፊት ሕዝብ እንዳለው ከእግዚአብሔር በመስማት አረጋገጠ። አስተውሉ፣እግዚአብሔር በዚህ ብቻ አያቆምም። በመቀጠልም ሕዝቡ በግብፅ ውስጥ ስለገጠሙት ችግሮች ከሙሴ ጋር ተነጋገረ። እግዚአብሔር የሕዝቡን ጩኸት ሰምቶ በዚያም አንድ ነገር ሊያደርግ ነው። በፈርዖን ፊት ሕዝቡን እንዲወክል እንደመረጠው ለሙሴ ተናገረው። በዚያን ጊዜ በምድር ላይ በጣም ኃያል በሆነ መሪ ፊት ጉዳያቸውን የሚያቀርበው እሱ ይሆናል። እግዚአብሔር ሙሴ የእስራኤል ልጅ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ለዚያ ሕዝብ የእሱ ወኪል ይሆን ዘንድ አረጋገጠለት።

እኔ ስለ እናንተ አላውቅም፣ነገር ግን እኔ ሙሴን ብሆን እንደዚህ ላለው ተግባር ብቁ እንዳልሆንኩ እርግጠኛ ነኝ። በእርግጠኝነት ከሙሴ በተሻለ ሊወክላቸው ከሚችል ሰው ላለፉት ሰማንያ ዓመታት ከህዝቡ መካከል የኖረ ሰው መሆን አለበት። ለዚህ ወደ ሕይወቱ ለመጣው የእግዚአብሔር ጥሪ ሙሴ የሰጠውን ምላሽ አስተውሉ፡

11 ሙሴም እግዚአብሔርን፦ ወደ ፈርዖን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ? አለው። (ዘጸአት 3)

በዚያ ቀን በእግዚአብሔር ፊት ሲቆም ከዚህ ጥሪ ጋር ይታገል ነበር። ከዚህ በፊት የእስራኤል ሕዝብ ለአርባ ዓመት እርሱን አልተቀበሉትም ነበር። ግብፅ እንደ ነፍሰ ገዳይ እና ከሃዲ ትመለከተው ነበር። ስለመናገር ችሎታውን ጥያቄ አቅርቧል። ላለፉት አርባ ዓመታት እረኛ ስለነበር የአንድ ሀገር መሪ ለመሆን ብቁ እንደሆነ አልተሰማውም።

ወደ ሕይወቴ የመጣውን የእግዚአብሔርን ጥሪ ስመለከት እንደ ሙሴ የተሰማኝ ብዙ ጊዜያት ነበሩ። ቃሉን እጽፍ እና አስተምር ዘንድ እኔ ማን ነኝ? እግዚአብሔር እኔ የማዘጋጃቸው መጽሐፎች ተተርጉመው ወደ ተለያዩ አገሮች እንዲላክ ይፈቅድ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ይህን አገልግሎት ሊያገለግሉ የሚችሉ ከእኔ የበለጠ ብቃት ያላቸው የሚመስሉ በርካታ ሰዎች አሉ። መልሱ ሁልጊዜ እግዚአብሔር ወደጠራኝ ወደ እውነታው ይመልሰኛል። ወደ ሕይወቴ የመጣው የእግዚአብሔር ጥሪ እንጂ የእኔ ብቃት እንዳልሆነ ተገንዝቤአለሁ። ብቁ የሆንኩት በእኔ ልምድ ወይም ችሎታ ሳይሆን እግዚአብሔር ስለጠራኝ ነው። እኔ እንደ ሙሴ፣ለሥራው ብቁ እንዳልሆንኩ ይሰማኝ ነበር፣ ነገር ግን በሕይወቴ የእግዚአብሔር ጥሪ እና ዓላማ በመተማመን እወጣለሁ።

ሙሴን በቀጣዮቹ ዓመታት ስንመለከት፤ወደ ግብፅ እየተመለሰ ያለን ዓይናፋር ሰው እናስተውላለን። የእግዚአብሔርን መሪት እየተከተለ ለፈርዖን እና ለእስራኤል ሕዝብ ቃሉን ሲናገር እናያለን። ሙሴ ጥበብን እና ምሪትን ለመፈለግ በየጊዜው ወደ ጌታ ፊት ሲሄድ እንመለከታለን። እግዚአብሔር በሙሴ በኩል ሲሠራ እና ግብፅን ሲመታ እንዲሁም መላው ሕዝብ ከባርነት ነጻ ሲወጣ እናያለን። እስራኤላውያንን ወደ ደኅንነት ለመምራት የባሕሩ ውኃ ሲከፈል የእግዚአብሔር ተአምራዊ ኃይል ሲገለጥ እናያለን። ከሁለት ሚሊዮን ለሚበልጡ ሰዎች እና ለእንስሳዎቻቸው የእግዚአብሔርን ዕለታዊ አቅርቦትን እናስተውላለን። እግዚአብሔር ይህንን ሃገር አልባ ስደተኛ ሰው ሕዝቡን የሚተዳደሩበት ሕግጋት ወዳለው ሉዓላዊ ሃገር ለማቅናት ይጠቀምበታል።

ሙሴን ለሃገር ግንባታ ተግባር ብቁ ያደረገው ምንድ ነው? አገልግሎቱን ይህን ያህል ፍሬያማ ያደረገው ምንድን ነው? የእግዚአብሔር ምርጫ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው? በግብፅ ሃገር የነበረው ተጽዕኖ እንዳልሆነ ግልፅ ነው። እግዚአብሔር ያንን ከእርሱ ገፎታልና። እንዲሁም ከግብፅ ቅጣት አምልጦ ስለነበር እስራኤል ያለፈበት የባርነት መከራ አላጋጠመውም። የእስራኤላውያን ክብርን በማግኘቱም አልነበረም፤ምክንያቱም ከግብጻውያን እንደ አንዱ አድርገው ስለተመለከቱት አልተቀበሉትም ነበርና። በተፈጥሮአዊው ችሎታው የመጣ አልነበረም ምክንያቱም ወደዚህ አገልግሎት ከመጠራቱ በፊት ተፈጥሮአዊ ችሎታው በእድሜ መግፋት ምክንያት እስኪቀንስ እና ሰማንያዎቹ እድሜ ላይ እስኪደርስ ድረስ እግዚአብሔር ይጠብቀው ነበርና። ስለ አገልግሎት ፍሬያማነት ሰው የሚሰጣቸውን ምክንያቶችን ከልብ መፈለግ እንዴት ቀላል ነው። በመጨረሻ ግን በሙሴ ሕይወት የነበረው ፍሬያማ አገልግሎት ከማንኛውም የግል ብቃቶች ይልቅ ከእግዚአብሔር ጸጋ ጋር የሚገናኝ ነበር። እግዚአብሔር ለዚህ ተግባር ስለመረጠው ፍሬያማ ነበር። ሙሴ እግዚአብሔርን ጥሪ ለመቀበል እንኳን ፈቃደኛ አልነበረም። በእግዚአብሔር እና በሙሴ መካከል የተደረገውን ውይይት አዳምጡ፡

አሁንም ና፥ ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ታወጣ ዘንድ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ። (ዘጸአት 3:10)

ሙሴም እግዚአብሔርን፦ ወደ ፈርዖን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ? አለው። (ዘጸአት 3:11)

እርሱም፦ በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ… (ዘጸአት 3:12)

እግዚአብሔርም ሙሴን፦ያለና የሚኖርእኔ ነኝ አለው፤ እንዲህ ለእስራኤል ልጆች፦ያለና የሚኖርወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ አለው። (ዘጸአት 3:14)

እግዚአብሔርም ደግሞ ሙሴን አለው፦ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ፦ ‘እኔ እኔ ነኝ ‘(ዘጸአት 3:15)

ሙሴም መለሰ፦ እነሆ አያምኑኝም ቃሌንም አይሰሙም፦ እግዚአብሔር ከቶ አልተገለጠልህም ይሉኛል አለ። (ዘጸአት 4:1)

እግዚአብሔርም፦ ይህች በእጅህ ያለችው ምንድር ናት? አለው። እርሱም፦ በትር ናት አለ። ወደ መሬት ጣላት አለው፤ እርሱም በመሬት ጣላት፥ (እባብም ሆነች) (ዘጸአት 4:2-3)

ሙሴም እግዚአብሔርን፦ ጌታ ሆይ፥ እኔ አፌ ኰልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባሪያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም። (ዘጸአት 4:10)

እግዚአብሔርም፦ የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው? እንግዲህ አሁን ሂድ፥ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፥ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ አለው። (ዘጸአት 4:11-12)

እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ በምትልከው ሰው እጅ ትልክ ዘንድ እለምንሃለሁ አለ። (ዘጸአት 4:13)

ሙሴ ከፊቱ ላለው ሥራ ራሱን ብቁ ሆኖ እንዳላገኘው ትንሽ ጥርጣሬ ሊኖር ይችላል። በዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ባደረገው ክርክር፣ በራሱ ብቁ ስለመሆኑ እምነት አልተሰማውም፣ እግዚአብሔር ለሥራው የሚያስፈልገውን ሁሉ እየሰጠው ወደ እውነታው ማምጣቱን ቀጥሏል። ሙሴ እግዚአብሔር ለጥሪው እና ሥራው የሚያስፈልገውን አሟልቶ ስለሰጠው ስኬታማ ሆኗል። እግዚአብሔር ሙሴን የመረጠው ባሉት ምርጥ ብቃቶች ምክንያት አይደለም፤ሙሴ ስለዚህ ጉዳይ ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገው ንግግር በጣም ግልፅ ነው።

ሃገርን ለመገንባት እግዚአብሔር ስደተኛ እንዲመርጥ ያደረገው ምንድን ነው - ጸጋው ብቻ ነው። እግዚአብሔር መላውን ዓለም የሚባርክበትን ታላቅ ሕዝብ ለመምራት የተሰበረውን ሰው መጠቀምን መረጠ። ለሙሴ ኃይል የሰጠው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። ወዴት መሄድ እንዳለበት ሳያውቅ የሚያስፈልገውን ጥበብ የሰጠው ጸጋው ነው።

እንዲህ ባለው ፍሬያማ አገልግሎት ሙሴን ለመባረክ እግዚአብሔር ላይ ተጽዕኖ ያደረገውን ነገር በሙሴ ህይወት ውስጥ ለማግኘት የምንፈልገውን ያህል፣እውነታው ሙሴ ነገሮችን በዚህ መንገድ አለማየቱ ነው። ብቁ እንዳልሆነ ተሰምቶት ነበርና። እግዚአብሔር በጸጋው እንደ አምባሳደር እና የአንድ ሃገር መሪ አድርጎ የመረጠው ቤት አልባውን ስደተኛ ነበር።

 

ለምልከታ፡

•              ሙሴ ከገዛ ወገኖቹ እንዴት ተወሰደ?

•              ሙሴ ግብጻዊ ሆኖ በማደጉ ደስተኛ ነበር? የእሱ ታማኝነት የት ነበር?

•              እስራኤል ሙሴን እንዴት ይመለከተው ነበር?

•              ሙሴ በምድያም ምድር ሲኖር ምን ይሰማው እንደነበር የበኩር ልጁ ስም ምን ያመለክታል?

•              ሙሴ የእግዚአብሔርን ጥሪ ለመቀበል ብቁ ሆኖ ተሰማውን? አብራሩ።

•              የሙሴ ብቸኛው ትክክለኛ መመዘኛ በሕይወቱ የመጣው የእግዚአብሔር ጥሪ ብቻ ነው ማለት ትክክል ይሆናልን? ይህ በቂ ነበር?

•              ለመንግሥቱ ፍሬያማ እንዲያደርገን ከራሳችን አንድ ነገር መፈለግ እንደሚያስፈልገን የሚሰማን ለምንድ ነው? የሙሴ ፍሬያማ አገልግሎት በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረው የንጹህ ጸጋ ተግባር እስከ ምን ድረስ ነበር?

ለጸሎት፡

•              እኛ የማንቀበላቸውን ሰዎች ለመጠቀም ፈቃደኛ በመሆኑ ጌታን ለማመስገን ትንሽ ጊዜ ውሰዱ።

•              በሕይወቱ የእግዚአብሔርን ጥሪ ለመቀበል ሲታገል ለነበረው ሙሴ ስላሳየው ትዕግሥት ጌታን አመስግኑ። በሕይወታችሁ ከመጣው ከእግዚአብሔር ጥሪ ጋር ታግላችኋልን?

•              እግዚአብሔር ለሰጠን አገልግሎት በተፈጥሮ ብቁ ባንሆንም፣እርሱን ለማገልገል የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሚሰጠን በእርሱ በመታመን ጌታን አመስግኑት።

•              በሕይወታችሁ ወደ መጣው ወደ እርሱ ጥሪ ለመውጣት እንድትችሉ ጌታ ጸጋ እንዲሰጣችሁ ጸልዩ።


ምዕራፍ 3 - በቀለኛው ብርቱ ሰው እና የእስራኤል ጠላቶች ሽንፈት

አንዳንድ ጊዜ መንግሥቱ ላይ ኃይለኛ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ ሰዎች ወደ ጌታ መቅረብ እንዳለባቸው ይሰማናል፣አለበለዚያ እንዴት በአገልግሎት ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ ሃሳብ ስኬትን ከታማኝነት ጋር አቆራኝቶ ይገልጻል። እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ አንድ ነገር ስለተመለከተ ይጠቀምብናል ከሚል ስሜት የመጣ ነው። በአገልግሎት ውስጥ ፍሬያማነት የእኛ መልካም ጥረት ወይም በስጦታዎች እና ተሰጥኦዎች አጠቃቀም ምክንያት የምናገኘው ነገር ሳይሆን የእግዚአብሔር ጸጋ ተግባር መሆኑን ማየት ይሳነዋል። እስቲ በእስራኤል ውስጥ ሳምሶን የተባለውን የአንድ መሳፍንት ሕይወት እንመልከት።

ሳምሶን የተወለደው ፍልስጤማውያን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ከባድ ችግር እየፈጠሩ በነበረበት ወቅት ነበር። መሳፍንት 13:1 የሚናገረውን አዳምጡ፡

1 የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ፤ እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን እጅ አርባ ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው። (መሣፍንት 13)

ይህ ጥቅስ ሳምሶን ይኖርበት በነበረው ዘመን ሁለት ነገሮችን ያሳየናል። አንደኛ፣ የእስራኤል ሕዝብ ከጌታ እግዚአብሔር በመፍራት አይመላለስም ነበር። ሁለተኛ፣ በኃጢአታቸው ምክንያት የእግዚአብሔር ፍርድ በእነርሱ ላይ ነበር። ይህ ለአርባ ዓመታት ያህል ሲጨቁኗቸው በነበሩት ፍልስጤማውያን መልክ የመጣ ነበር።

ሳምሶን የተወለደው ስሟ በመጽሐፍ ቅዱስ ባልተጠቀሰ ሴት ነው። እርሷም የማኑሄ ሚስት ነበረች። የማኑሄ ሚስት መካን ነበረች ነገር ግን አንድ ቀን የጌታ መልአክ ተገልጦላት እንደምትፀንስና ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ነገራት (መሳፍንት 13: 3) መልአኩ ለሳምሶን እናት ይህ ልጅ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለጌታ ተለይቶ እንደሚኖር ነገራት።

3 የእግዚአብሔርም መልአክ ለሴቲቱ ተገልጦ እንዲህ አላት፦ እነሆ፥ አንቺ መካን ነሽ፥ ልጅም አልወለድሽም፤ ነገር ግን ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። 4 አሁንም ተጠንቀቂ፤ የወይን ጠጅን የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ። 5 እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ እርሱም እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ማዳን ይጀምራል።

የማኑሄ ሚስት ይህ የልጅዋ መለየት ለሕይወት ዘመን ሁሉ እንደሚሆን በመረዳት ለባሏ የነገረችው በጣም ግልፅ ነው፡

7 እርሱም፦ እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ እስኪሞት ድረስ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና አሁን የወይን ጠጅ የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ አለኝ ብላ ተናገረች። (መሣፍንት 13)

እግዚአብሔር በሳምሶን ላይ ያኖረውን ልዩ መለያዎችን አስተውሉ። በመጀመሪያ፣ የወይን ጠጅ የሚያሰክርም ነገር በጭራሽ አይጠጣም። ሁለተኛ፣ርኩስ የሆነ ነገር ፈጽሞ አይበላም። ሦስተኛ፣በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት  እነዚህ ለጌታ የመለየቱ ምልክቶች ነበሩ፤ስለሆነም ሳምሶን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በእነዚህ መመዘኛዎች እንዲኖር ይጠበቃል። ጌታ ለሳምሶን በጣም የተለየ ዓላማ እንዳለው ከመልአኩ ቃል አስተውሉ። እሱ እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ለማዳን ሳምሶንን ሊጠቀም ዓላማ ነበረው። ሳምሶንም ለዚህ ዓላማ የተወለደ ልዩ ልጅ ነበር።

ሳምሶን ሲያድግ ወደ ፍልስጥኤማውያን ከተማ ወደ ተምና ወረደ። በእስራኤል ጠላቶች ከተማ ለምን እንደነበረ አልተነገረንም፤ዳሩ ግን እዚያ በነበረበት ጊዜ እርሱን በፍቅር የሳበች አንዲት ፍልስጥኤማዊ ሴት አገኘ። ወደ እስራኤል በመመለስ ለአባቱ እና እናቱ ሊያገባት እንደሚፈልግ ነገራቸው። ይህም የወላጆቹን ልብ አሳዘነ። እስራኤላውያን ወንዶች ባዕድ ሚስቶችን ማግባት አይገባቸውምና። ፍልስጤማውያን የእስራኤል ጠላቶች ስለነበሩ እና ሳምሶን ደግሞ ከዚህ ጠላት እንደሚያድናቸው የጌታ መልአክ አስቀድሞ ነግሯቸው ስለነበር ይህ ጉዳይ ወላጆቹን የበለጠ አሳሰበ። እዚህ ሳምሶን ጠላቱን ለማግባት ሲፈልግ እንመለከታለን። ይህም ጠላትን የቤተሰቡ አባል ያደርጋል። በዚህ ጉዳይ ላይ እግዚአብሔርን አለመታዘዝ ጥሩ ነገር ሊሆን እንደሚችል ወላጆቹ አላዩም ነበር።

በዚህ ጋብቻ ላይ ስጋት ቢኖራቸውም፣የሳምሶን ወላጆች የወጣት ፍልስጤማዊቷን ቤተሰብ ለማነጋገር አብረውት ሄዱ። በመንገዳቸው ላይ የአንበሳ ደቦል እያገሳ ወደ እርሱ ደረሰ፤ ሳምሶንም፤ በባዶ እጁ ገድሎ ቆራረጠው (መሳፍንት 145-6 ተመልከቱ) ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሲመለስ ሳምሶን የገደለውን የአንበሳ አካል ለማወቅ ጓጉቶ ነበር። ፈልጎም ሄዶ አገኘው። በዚህ የሞተ አንበሳ አካል ውስጥ የንብ መንጋ ተመልክቶ ሳምሶን ማርን በእጆቹ ወስዶ መንገዱን ቀጠለ። ጥቂት ማር ለወላጆቹ ሰጠ ነገር ግን ከሞተ አንበሳ አስከሬን እንደ ወሰደው አልነግራቸውም (መሳፍንት 149 ተመልከቱ)

በዚህ ረገድ ጉልህ የሆነው ነገር ሳምሶን የሞተውን እንስሳ አካል መንካቱ ነው። ናዝራዊ ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት ሲለይ የተሰጠው አንዱ ግዴታ ርኩስ ነገር እንዳይነካ ነው። ይህ የሞተ እንስሳ ርኩስ ነበር። ማርን ከየት እንዳገኘ ለወላጆቹ ያለመናገሩ እውነታ ቃል ኪዳኑን በእግዚአብሔር ፊት እንደሚያፈርስ በማወቁ ምክንያት እንደሆነ ሊጠቁም ይችላል። ይህ እሱን የሚያሳስበው አይመስልም።

ሳምሶን ቃል ኪዳኑን በቁም ነገር አለመውሰዱ ብቻ ሳይሆን ይህን ቃል ኪዳን በማፍረሱ የተደሰተ ይመስላል። ቤተሰቡ በተምና ጋብቻውን ሲያከብሩ ሳምሶን እና ሠላሳ ጓደኞቹ በአንድነት እየበሉ ነበር። ሳምሶን ከእነርሱ ጋር ውርርድ አደረገ። እንቆቅልሹን መፍታት ከቻሉ ለእያንዳንዳቸው ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ እንደሚሰጣቸው ነገራቸው። ካልቻሉ እያንዳንዳቸው ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ ይሰጡታል

እንቆቅልሹ በጣም ቀላል ነበር፡

14 እርሱም፦ ከበላተኛው ውስጥ መብል ወጣ፥ ከብርቱም ውስጥ ጥፍጥ ወጣ አላቸው። ሦስት ቀንም እንቈቅልሹን መተርጎም አልቻሉም። (መሣፍንት 14)

ሳምሶን ለእግዚአብሔር የገባውን ቃል በማፍረሱ ኩራት የተሰማው ይመስላል። በዚህ ክፍል እሱ ከሠራው ነገር ተነስቶ ቀልድ ሲቀልድ እንመለከታለን። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ ቃል ኪዳናቸውን በቁም ነገር የወሰዱ ሰዎች ይህንን እንደ ቀልድ አያዩትም። እዚህ ሳምሶን የሚያፍርበት ምንም ስሜት የለውም።

የእንቆቅልሹን መልስ ለማግኘት የሳምሶን ጓደኞች እጮኛውን እና ቤተሰቦቻቸውን እንደሚገድሉ አስፈራሩ። መልሱን እንዲነግራት ሳምሶንን ስትገፋው እሱም ነገራት። እሷም ለጓደኞቹ ነገረቻቸው፤ ከዚያም የእንቆቅልሽ መልሳቸውን የሚመልሱበት ቀን ሲደርስ ጥያቄዎቹን በትክክል መለሱ። ውርርዱን ለመክፈል ሳምሶን ወጥቶ ሠላሳ ፍልስጤማውያንን ገድሎ ልብሳቸውን ለጓደኞቹ ሰጠ። በእጮኛዋ እና በጓደኞቹ በመታለሉ ተቆጥቶ ፍልስጤምን ትቶ ወደ ቤቱ ተመለሰ።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሳምሶን ወደ ፍልስጤም ወደ እጮኛው ተመለሰ። ጋብቻውን ለማድረግ ዝግጁ በመሆን፣ እሷን ለማግኘት ወደ አባቷ ዘንድ ሄደ። አባቷ ግን ከሳምሶን ጓደኞች ለአንዱ ሚስት አድርጎ ድሯት ነበር። ሳምሶን በአማቱ በጣም ስለተናደደ ሄዶ 300 ቀበሮች ያዘ፤ ችቦም ወስዶ ሁለት ሁለቱንም ቀበሮዎች በጅራታቸው አሰረ፥ በሁለቱም ጅራቶች ማካከል አንድ ችቦ አደረገ።ችቦውንም አንድዶ በቆመው በፍልስጥኤማውያን እህል መካከል ሰደዳቸው፤ ነዶውንም የቆመውንም እህል ወይኑንም ወይራውንም አቃጠለ።

ሳምሶንን ያነሳሳው በቀል ነበር። ያደረገው ነገር በፍልስጥኤማውያን ልብ ውስጥ ብዙ ቁጣ ቀስቅሶ ስለነበር፤ሊዋጉት ሦስት ሺሕ ሠራዊት ላኩበት። ከዚያም አዲስ የአህያ መንጋጋ ወስዶ፥ ተዋጋቸውም፥ በዚያን ቀን አንድ ሺህ ፍልስጤማውያንን ሰው ገደለ። የእስራኤል ሕዝብ፣የሳምሶንን ታላቅ ጥንካሬ እና ፍልስጤማውያንን ለማሸነፍ ያለውን ፍላጎት ተገንዝበው፣በእነርሱ ላይ አለቃ አድርገው ቀቡት- ሳምሶን ለሃያ ዓመታት በእስራኤል ላይ የሚፈርድበት የስልጣን ወንበር ነው (መሳፍንት 15:20 ተመልከቱ)

የእስራኤል መሪ እንደመሆኑ መጠን የሳምሶን የስነ ምግባር ሕይወት ብዙ የሚፈለግ ነበር። በመሣፍንት 16:1 ሳምሶን ሴተኛ አዳሪ አይቶ ወደ ፍልስጤም እንዴት እንደሄደ እና ከእርሷ ጋር እንደተኛ እንመለከታለን። ከፍልስጤማዊው ጋለሞታ ጋር በመተኛት በጠላት ግዛት ውስጥ ሳምሶን ምን እያደረገ እንደነበረ ያስደንቀናል። ይህ በእስራኤል ውስጥ ውርደትን መፍጠር ብቻ ሳይሆን የፍልስጥኤማውያንን ቁጣ ቀስቅሷል። የጋዛ ሰዎች ሳምሶን ወደ ከተማቸው መጥቶ ከአንዲት ዝሙት አዳሪአቸው ጋር መተኛቱን በሰሙ ጊዜ እሱን ለመግደል በማሰብ ቤቱን ከበቡት። ሳምሶን ግን ሳይታወቅ ከከተማዋ አምልጦ ሄደ።

ይህ ብዙም ሳይቆይ ሶምሶን በሶሬቅ ሸለቆ ውስጥ የምትኖር ፍልስጤማዊቷን ሴት ወደደ። ስሟም ደሊላ ይባላል። ከእሷ ጋር ገባ። አሁንም፣የእስራኤሉ አለቃ ለምን በእስራኤል ውስጥ እንደማይኖር፣ነገር ግን ከፍልስጤማዊቷ ሴት ጋር ለመኖር ለምን መረጠ የሚለው ያስደንቀናል። ይህ በእስራኤል ዘንድ ግራ መጋባት ሊፈጥር እንደሚችል መገመት እንችላለን። ሳምሶን በጠላት ግዛት ውስጥ መገኘቱ ለፍልስጥኤማውያን የጎን እሾህ ነበር። እርሱን ለመግደል ያለማቋረጥ እየሞከሩ ነበር። ይህ ጥቃቶቻቸውን ዘንግቶ የሚመስለው ሳምሶንን የሚረብሽ አይመስልም።

ሆኖም በደሊላ ማታለል ምክንያት ሳምሶን በመጨረሻ እስረኛ ሆነ። የታላቁን ጥንካሬ ምስጢር ከነገራት በኋላ ፀጉሩን ላጨችው ከዚያም ጠላቶቹ እንዲይዙት ጋበዘቻቸው። እነርሱም ዓይኖቹን አወጡት። ሳምሶን እስር ቤት ውስጥ እንደታሰረ፣ የጥንካሬው ምስጢር የነበረው ጸጉሩ ተመልሶ ያድግ ጀመር። ፍልስጥኤማውያን ወደ አምላካቸው ለዳጎን ክብረ በዓል ወቅት እንዲያዝናናቸው ሲወስዱት ሳምሶን ሁሉም ሰው ወደተሰበሰበበት ወደ ታላቁ ቤተ መቅደስ ዓምዶች እንዲመራው አንድን ወጣት ጠየቀ።

በመሣፍንት 1628 ሳሞሶን ወደ እግዚአብሔር እንደጮኸ እናባለን፡

28 ሶምሶንም፦ስለ ሁለቱ ዓይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አሁን እንድበቀል፥ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ እባክህ፥ አስበኝ፤ አምላክ ሆይ፥ ይህን አንድ ጊዜ ብቻ፥ እባክህ፥ አበርታኝ ብሎ እግዚአብሔርን ጠራ። (መሣፍንት 16)

ሳምሶን ወደ እግዚአብሔር የጮኸበት ብቸኛው ጊዜ ይህ ይመስላል። ልብ በሉ፣ እርሱ የጥንካሬው ምንጭ እግዚአብሔር መሆኑን ያውቃል። ሆኖም፣ ከዚህ ፍላጎት በስተጀርባ ያለው ፍላጎት ዓይኖቹን በማውጣታቸው ምክንያት ጠላቶቹን ለማጥፋት በቀል መፈለጉ ነው። በእነዚህ የመጨረሻዎቹ የሳምሶን ቃላት ውስጥ የእግዚአብሔር ክብር አልተጠቀሰም። ወይም ስለ ሕዝቡ መዳን የሚጨነቅ አይመስልም። የንስሐ ጸሎትም አልጸለየም። ሳምሶን ወደ እግዚአብሔር የጮኸው እሱ ለሚያገለግላቸው ሰዎች ሳይሆን ለራሱ ነበር።

እግዚአብሔር ያንን ጸሎት መለሰ፤ከዚያም በዳጎን ቤተመቅደስ ውስጥ የነበረውን ሁለት ዓምዶችን ገፍቶ ሳምሶን ሕንፃውን በእሱ እና በዚያ በነበሩት ሁሉ ላይ አፈረሰው። ሳምሶን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ከገደለው በላይ በዚያ ቀን በርካታ ፍልስጤማውያንን ገደለ (መሳፍንት 1630) ለሳምሶን እናት የተነገረው ትንቢት እውን ሆነ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ከፍልስጥኤማውያን ለማዳን ልጇን ተጠቅሟል።

እግዚአብሔር በዚያ ቀን የተጠቀመበትን ሰው ተመልከቱ። ሳምሶን ለጌታ የገባውን ቃል ችላ ያለ ሰው ነበር። ይህም ቃሉን ስለማፍረሱ ብቻ ሳይሆን በማፍረሱም ምክንያት ይቀልድ ነበር። ከባዕዳን ሴቶች ሚስት በመፈለግ የእግዚአብሔርን ሕግ ተላልፏል። እንዲሁም ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር ይተኛ ነበር፣ ሚስቱ ካልሆነች ሴት ጋር ይኖር ነበር። ያለ ምንም ጸጸት ወይም ንስሐ ይኖር ነበር። ሳምሶን ሲናደድ በጣም ጨካኝና በበቀል የተሞላ ይሆናል። ስለ እግዚአብሔር ሃሳብ ደንታ የሌለው እና ለራሱ ብቻ የሚያስብ ግለሰብ ነበር። ይህም ጌታን የሚፈታተን በሚመስልበት ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። በሕይወቱ ውስጥ የወሰናቸው ውሳኔዎች ሁሉ ለሕዝቡ ወይም በሕይወቱ ለመጣው የእግዚአብሔር ጥሪ አክብሮት ያሳየ አልነበረውም።

በስተመጨረሻም በዚህ ሁሉ ክፋት ተያዘ። አብሯቸው የተኛቸው ሴቶች ሁሉ ጠላት ሆኑበት። የፈተዋጋቸው ፍልስጤማውያን ዓይኖቹን አወጡት። የእግዚአብሔርን ሕግ አለማክበሩ ዓይነ ስውር እስረኛ ሆኖ የሕይወቱ ፍጻሜ ሲደርስ ተመልክተናል። እነዚህ ነገሮች ቢኖሩም፣እርሱ ሕዝቡን ከፍልስጥኤማውያን ጭቆና ለማዳን የእግዚአብሔር መሣሪያ ነበር።

እንደ ሳምሶን ያለ መጋቢ ለቤተክርስቲያናችሁ ትቀጥራላችሁን? የእናንተ የወንጌል ተልዕኮ ሥራ መሪ እንዲሆን ትቀበሉታላችሁን? እግዚአብሔር እንዲሰራ በጠራው ሥራ ውስጥ የስኬቱ ምስጢር ምን ነበር? በእርግጥ በኑሮው እግዚአብሔርን የሚፈራ አልነበረም። ወይም በባህሪው ትሑት አልነበረም። ሳምሶን በርካታ ጉድለቶች ቢኖሩበትም ለአገልግሎቱ ስኬት ብቸኛው ማብራሪያ የሚሆነው እግዚአብሔር ሊጠቀምበት መወሰኑ