የወንጌል አጋሮች

መጽሐፍ ቅዱስ ወንዶች እና ሴቶች በቤተክርስቲያን ስለሚኖራቸው ሚና የሚያስተምረውን መመርመር

 

ኤፍ. ዋይኒ ማክ ሌዎድ

 

Light to My Path Book Distribution
Sydney Mines, NS, CANADA B1V 1Y5


የወንጌል አጋሮች

የቅጂ መብት © 2018 በኤፍ. ዋይ ማክ ሌዎድ

መብት ሁሉ የተጠበቀ ነው፡፡ከጸሐፊው የጽሑፍ ፈቃድ ውጪ፤የትኛውም የዚህ መጽሐፍ አካል በማንኛውም መልክ ወይም መንገድ ሊሰራጭ ወይም ሊተላለፍ አይችልም።

በዚህ መጸሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ እትሞች ተወስደዋል፤      “Holy Bible, New International Version®, NIV®. Copyright© 1973, 1978, 1984, 2011 by Biblica, Inc.™ Used by permission of Zondervan. All rights reserved worldwide. www.zondervan.com The “NIV” and “New International Version” are trademarks registered in the United States Patent and Trademark Office by Biblica, Inc.™

“Scripture quotations marked (ESV) are from the ESV® Bible (The Holy Bible, English Standard Version®), copyright © 2001 by Crossway, a publishing ministry of Good News Publishers. Used by permission. All rights reserved.”

Scripture quotations from The Authorized (King James) Version. Rights in the Authorized Version in the United Kingdom are vested in the Crown. Reproduced by permission of the Crown’s patentee, Cambridge University Press

ትርጉም፡ በሔኖክ እስጢፋኖስ


 

ማውጫ

መግቢያ. 5

ፍጥረት እና ውድቀቱ.. 9

የብሉይ ኪዳን አምልኮ. 21

ኢየሱስ እና ሴቶች.. 43

የጥንቷ ቤተክርስቲያን. 55

የሐዋሪያው ጳውሎስ ትምህርት 1 ቆሮንቶስ 11  73

የሐዋሪያው ጳውሎስ ትምህርት 1 ቆሮንቶስ 14  91

የሐዋሪያው ጳውሎስ ትምህርት 1 ጢሞቴዎስ 2  105

የአተገባበር መርሆች.. 117


 

መግቢያ

በቤተክርስቲያን አገልግሎት የሴቶች ሚና ለብዙ ዓመታት አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። በጉዳዩም ላይ ብዙ መጻሕፍት ተጽፈዋል። ሴቶች በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ስላላቸው ሚና የሚነሱ ክርክሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ እና ማኅበራዊ ተፈጥሮ ያላቸው ናቸው።

በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ስለ ሴቶች የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንብበው ለሁሉም ባህሎች እና ጊዜያት ቃል በቃል ትርጉም የሚሰጡ ሰዎች አሉ።                    ሌሎች ደግሞ ሴቶች እንደ እኛ ዘመን ያልተማሩ እና ነጻ ባልሆኑበት ዘመን የነበረውን ባህል ተግባራዊ ሊያደርጉ ጽሑፎችን ይመለከታሉ። በዚህም ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጊዜው ያለፈበት እና ለዛሬዋ ቤተክርስቲያናችን የማይጠቅም ነው እስከማለት የደረሱ አሉ። ስለዚህ ጉዳይ ያለኝን አቋም በዚህ ጥናት መጀመሪያ ላይ ልንገራችሁ።

 

በመጀመሪያ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለሁሉም ባህሎች እና ጊዜያት በስልጣን እንደሚናገር አምናለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ ያለፈበት አይደለም። ኢየሱስ ያስተማረው ትምህርት በጻፉት ሐዋርያት ላይ እንደሠራው ሁሉ በእኛም ዘመን በእኛ ላይ ይሠራል። እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን ያለውን ዓላማ በቃሉ ገልጿል። እርሱ እስኪመለስ ድረስ ቃሉን በትምህርት እና በተግባር መሪ አድርጎ ሰጥቶናል። በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የቀረቡት መርሆች በሁሉም ባሕሎች ላይ ይሠራሉ።

የእነዚያ መርሆዎች አተገባበር ከባህል ወደ ባህል ሊለያዩ ይችላሉ፤ነገር ግን ሁሉም ባህሎች በሁሉም ጊዜያት  የእግዚአብሔር ቃል በሚያስተምረን እውነት መመላለስ ይጠበቅባቸዋል። በሁሉም የአስተምህሮ እና የክርስትና ህይወት ጉዳዮች ላይ ያለው የእኛ ስልጣን ነው። በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ የሴቶችን ሚና የምንረዳ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መለኪያችን እና የእግዚአብሔር ስልጣን መሆኑን መገንዘብ አለብን።

 

በሁለተኛ ደረጃ፣ የሚያስተምረንን ብንወደውም ባንወድውም ቃሉን እንድንታዘዝ እግዚአብሔር ይጠብቅብናል። ልንታዘዝ የምንፈልገውን መርጠን መውሰድ አንችልም። እዚህ ላይ አንድ እውነት ልናገር። በአገልግሎት ውስጥ ሴቶች ሊኖራቸው ስለሚገባው ቦታ ምን እንደሚሰማኝ ብትጠይቁኝ ሁለት መልስ ልሰጣችሁ እችላለሁ።

 

በአንድ በኩል የእኔን የግል ልምድ እና ግንዛቤ መሰረት በማድረግ ሀሳቤን ልነግራችሁ እችላለሁ፡፡ እኔ ከማውቃቸው የወንድ ሰባኪዎች በተሻለ ስለሚሰብኩ እና ስለሚያስተምሩ ሴቶች ልነግራችሁ እችላለሁ። ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው ሴቶች በህይወቴ እና በእምነቴ ላይ ስላላቸው አስደናቂ ተጽእኖ መናገር እችላለሁ። አቅም እና ችሎታ ባላቸው ሴቶች የሚመሩ የንግድ ድርጅቶች እና ሃገራት ምሳሌዎችን ልጠቁማችሁ እችላለሁ። ወንድና ሴት በእኩልነት በእግዚአብሔር ፊት እንደሚቆሙ ልነግራችሁ እችላለሁ። እግዚአብሔር ለሴቶች የሰጣቸውን አስደናቂ ስጦታዎች ላስታውሳችሁ እችላለሁ፣ ይህም ደግሞ በክርስቶስ አካል ውስጥ ጥቅም ላይ መዋል አለበት።

 

በሌላ በኩል ደግሞ፣ በቀጥታ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ልወስዳችሁ እችላለሁ። ተቀምጠን ስለ ጳውሎስ ትምህርትና ስለ ኢየሱስ ምሳሌ መወያየት እንችላለን። ይህን ስናደርግ ራሴን ግራ መጋባት ውስጥ አገኘው ይሆናል። የጳውሎስ ትምህርት ከእኔ የግል አስተያየት ጋር ይስማማልን? ሴቶች በአገልግሎት ውስጥ ስለሚኖራቸው ሚና ከእሱ ጋር እስማማለሁን? እውነቱን ለመናገር፣ የእኔ አስተያየት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ጋር የሚጋጭ ሆኖ ያገኘሁበት ጊዜ አለ። ከመጽሐፍ ቅዱስ የማየውን ሳልቀበል ምን ማድረግ ሊኖርብኝ ነው? የቅዱሳት መጻሕፍትን ትምህርት በጥንቃቄ ከመረመርኩ በኋላ፣የጌታ ኢየሱስ ተከታይ እንደመሆኔ፣ግዴታዬ ለሱ መገዛት እና ከራሴ በላይ የእግዚአብሔርን መንገድ መቀበል ይሆናል።

 

በሦስተኛ ደረጃ፣ መጽሐፍ ቅዱስን በአግባቡ ለመረዳትና ተግባራዊ ለማድረግ ከፈለግን የተጻፉበትን ዘመን ባህል ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለብን መገንዘብ አለብን። በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ እኛን በመርህ ደረጃ ብቻ የሚመለከቱ ትዕዛዛት እና ትምህርቶች አሉ። ለምሳሌ በዘሌዋውያን 1927 ላይ የእግዚአብሔር ህግ ጢምን እና የፀጉርን ጎን መቁረጥን እንደሚከለክል እናነባለን። ሰው ፂሙን ቢቆርጥ ስህተት ነውን? ወደዚህ ጽንፍ መሄድ መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ መተርጎም ነው። እነዚህ ሕጎች የተጻፉት በብሉይ ኪዳን ዘመን ከነበሩት አረማዊ ሃይማኖታዊ ልማዶች አንፃር ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ የእነዚህን አረማዊ ባሕሎች እና ልማዶችን እንዳይኮርጁና ከእግዚአብሔር እንዳይርቁ ለማድረግ ታስቦ የተደረገ ነበር። በሙሴ ዘመን እንደነበረው ጢምን የመቁረጥ ልማድ ዛሬ እንቅፋት አይሆንም። በዘመናችንም እንዳለነው እንደ አዲስ ኪዳን አማኞች ይህ ተግባር ከእኛ የሚጠበቅ አይሆንም።

 

ሴቶች በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ያላቸውን ሚና በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ስንመረምር፣ ከላይ የተጠቀሱትን ሦስቱን መርሆች ተግባራዊ ማድረግ አለብን። የእግዚአብሔርን ቃል በቅንነት ልንመለከተው ይገባል። ጊዜው ያለፈበት አይደለምና፡፡ ወደድንም ጠላንም በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ያነበብነውን ለመታዘዝ ራሳችንን መስጠት አለብን። በመጨረሻም ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈበትን የባህል አውድ ወደ ጎን በመተው በተሳሳተ መንገድ እንዳንተረጎም መጠንቀቅ አለብን። እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንደ መመሪያችን ይዘን በዚህ አስቸጋሪ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትምህርት እንመርምር።

 

 

ኤፍ. ዋይኒ ማክ ሌዎድ


 

ምዕራፍ 1 -ፍጥረት እና ውድቀቱ

የሐዋርያት እና የአዲስ ኪዳን አማኞች የዓለም እይታ የተመሰረተው በአይሁድ እምነት ላይ ነው፤እርሱም ስለ እግዚአብሔር እና ፍጥረት ያለው ግንዛቤ ነው። ልንነሳበት የሚገባው የባህል እይታ ይህ ነው። ዘፍጥረት 1-3 የወንድና ሴት አፈጣጠር ታሪክን የሚተርክ ሲሆን እግዚአብሔር ለእነሱ ስላለው ዓላማ አንዳንድ ቁልፍ ዝርዝሮችን ይሰጠናል።

 

ዘፍጥረት 1 እናነባለን፡

 

26 እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።

27 እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።

28 እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው። (ዘፍጥረት 1)

 

ይህ ክፍል አጽንዖት ልንሰጣቸው የሚገቡ በርካታ ዝርዝሮች አሉት።

 

በመጀመሪያ፣ እግዚአብሔርሰውንበራሱ አምሳል እንደፈጠረ አስተውሉ። በዚህ ጥቅስ ውስጥ የተጠቀሰው "ሰው" የሚለው ቃል "አዳም" የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል የሚወክል ነው፤ እሱም ፆታን ወይም ወንድን ሳይሆን ሰውን ብቻ የሚያመለክት ነው፡፡ ይህንንም በቁጥር 27 ላይ ስናነብ ግልጽ ይሆናል፡

 

27 እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። (ዘፍጥረት 1)

 

በቀላል አነጋገር እግዚአብሔር ወንድና ሴትን አድርጎ ፈጠራቸው።

 

ማስተዋል የሚገባን ወንድ እና ሴት በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ መሆናቸው ነው። ይህም እነርሱን ከእንስሳት ለይቷቸዋል። በዚህ አምሳል ውስጥ እኩል ተሳታፊ ነበሩ።                  በስነ ሕይወት አፈጣጠራቸው ልዩነት ቢኖራቸውም ወንድ እና ሴት ሆነው ሲፈጠሩ ሁለቱም የእግዚአብሔርን መልክ እንዲያንጸባርቁ ነው። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ በመሆናቸው ሁለቱም ይህን የሚያሳይ ምስጋና እና ክብር ሊሰጣቸው የተገባ ነበር። በወንድ ወይም ሴት ላይ ክብር እና ምስጋና የጎደለው ድርጊት መፈጸም በሕይወታቸው ላይ የራሱን ምስል ያሰፈረውን እግዚአብሔርን መስደብ ነው።

 

በሁለተኛ ደረጃ ከዘፍጥረት 126-28 ላይ እግዚአብሔር ወንዱን እና ሴቲቱን በምድር ላይ ይገዙ ዘንድ እንደ ሰጣቸው አስተውሉ፡

 

26 እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። (ዘፍጥረት 1)

 

እግዚአብሔርም ወንድና ሴትን በአምሳሉ ከፈጠረ በኋላይግዙአቸውበማለት ይናገራል። የብዙ ቁጥር አጠቃቀሙ አስፈላጊ ነው። በምድር እና እንስሳት ላይ ያለው የበላይነት ወደ ወንድ እና ሴቲቱ ተላልፏል። በሌላ አነጋገር አዳምና ሔዋን ምድርን የመንከባከብ እና የማስተዳደር ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። እግዚአብሔር የሰጣቸውን ምድር ለመንከባከብ እንደ ወንድና ሴት አብረው ይሠራሉ።

 

በመጨረሻ በዘፍጥረት 128 ላይ እግዚአብሔር ለወንዱ እና ሴቲቱ የሰጠው ኃላፊነት ተባዝተው ምድርን እንዲሞሏት መሆኑን ልብ በሉ።

 

እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው። (ዘፍጥረት 1)

 

እኚህ የመጀመሪያ የሆኑት ወንድና ሴት አንድ ላይ በመሆን ልጆችን ወልደው ምድርን በሰው ልጆች መሙላት ነበረባቸው። እግዚአብሔር የሰው ልጆች ለመዋለድ እያንዳንዳቸው አንድ ላይ መሆናቸው በማያስፈልግበት መንገድ ሊፈጥር ይችል እንደነበር እወቁ፣ነገር ግን አላደረገውም። እርሱ ወንድና ሴት አድርጎ የፈጠራቸው እግዚአብሔር የሰጣቸውን ኃላፊነት ይወጡ ዘንድ አንዱ በሌላው ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ በማሰብ ነው። ወንድዬው ልጅ መውለድ አይችልም፡፡ ሆኖም ሴቲቱ ልጅን ተሸክማ ወደዚህ ዓለም ለማድረስ በሚያስችላት መንገድ ተፈጠች። ወተቷ ያንን ልጅ ጠጣር ምግብ መመገብ እስኪችል ወይም እስክትችል ድረስ ይመግበዋል ወይም ይመግባታል፡፡ እግዚአብሔር በሰጠው በዚህ የመባዛትና ምድርን የመሙላት ሥልጣን ውስጥ ወንድና ሴት የተለያየ ሚና ይኖራቸዋል።

 

በወንድና በሴት መካከል ያለው ልዩነት በሥነ ሕይወታዊ ልዩነታቸው ብቻ ሳይሆን በተፈጠሩበትም መንገድ ይታያል፡፡ በዘፍጥረት 27 መሰረት ሰው የተፈጠረው ከምድር አፈር ነው።

 

7 እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። (ዘፍጥረት 2)

 

የሴት አፈጣጠር ግን ከዚህ የተለየ ነበር። የተፈጠረችው ከአዳም ነው።

 

21 እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው። 22 እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት። 23 አዳምም አለ፦

ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤

እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።

 

ከዘፍጥረት 219 ጌታ እግዚአብሔር ወንድን፣እንስሳትን እና አዕዋፋትን ከመሬት እንደፈጠረ እንረዳለን፡

 

እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ከመሬት አደረገ፤ በምን ስም እንደሚጠራቸውም ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው፤ አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደ ጠራው ስሙ ያው ሆነ። (ዘፍጥረት 2)

 

ሴት ግን የተፈጠረችው ከመሬት ሳይሆን ከወንድ ነው። በዚህ አውድ ውስጥ ምን እየተከናወነ እንዳለ አስቡ። አዳም በገነት ውስጥ ሁሉንም ዓይነት እንስሳትና አዕዋፍ ሲያገኝ ቆይቷል። እግዚአብሔርም አዳምን ስም እንዲያወጣላቸው ጠየቀው። እነዚህ ሁሉ ፍጥረታት የተፈጠሩት ከምድር አፈር ነው። እግዚአብሔር ሴትን ከምድር አፈር ፈጥሮ ወደ ወንድ ቢያመጣት ኖሮ እንደ ሌላ ፍጥረት ይመለከታት ነበር።

እግዚአብሔር ከአዳም ጎን ሲያደርጋት፤አዳም ከጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ ሴቲቱን ለይቷት ነበር። እሷ እንደነሱ አልነበረችም ነበርና። እርስዋም ከእርሱ ስለ መጣች እንደ አዳም ነበረች።

 

አዳም ከጎኑ የጎድን አጥንት ተወስዳ መፈጠሯን እንዴት እንዳወቀ አልተነገረንም፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ሲነቃ ከእርሱ እንደመጣችና እንደ እርሱ መሆኗን እና በዙሪያው እንዳሉ እንስሶች እንዳልሆነች አወቀ። ይህ ድርጊት ሴቲቱን ከሌላው ፍጥረት ለይቷታል። ለወንድ አጋር ትሆን ዘንድ የተፈጠረች ናትና።

 

ስለ ወንድና ሴት አፈጣጠር ከሚገልጸው ዘገባ ልንመለከተው የሚገባ ሌላ ጠቃሚ ዝርዝር ነገር አለ። መጀመሪያ የተፈጠረው አዳም ነው። የልጆቻችን የትውልድ ሥርዓት ዛሬ ለእኛ ያን ያህል ትርጉም ባይኖረውም፣ በብሉይ ኪዳን የአይሁድ አውድ፣ ይህ የትውልድ ሥርዓት በጣም አስፈላጊ ነበር።

በኦሪት ዘኍልቍ 18 ላይ ያለውን የሙሴን ሕግ አድምጡ፡-

 

15 ከሰው ወይም ከእንስሳ ቢሆን፥ ለእግዚአብሔር ከሚያቀርቡት ሥጋ ሁሉ ማኅፀን የሚከፍት ሁሉ ለአንተ ይሆናል፤ ነገር ግን የሰውን በኵራት ፈጽሞ ትቤዠዋለህ፥ ያልነጻውንም እንስሳ በኵራት ትቤዠዋለህ። (ዘኍልቍ 18)

 

ማኅፀን የከፈተ በኩር ሁሉ የጌታ ነው እና ለካህኑ አገልግሎት ተሰጥቷል። በኩር ሆኖ የተወለደው እንስሳ ርኩስ ከሆነ ባለቤቱ ለካህኑ ዋጋውን ከፍሎ መልሶ በመግዛት ራሱ ጋር ያስቀረዋል። የበኩር ልጅ ወንድ ከሆነ ወላጆቹ በተወሰነ መጠን ከጌታ መልሰው በመግዛት ልጅ ከእነርሱ ጋር ይኖራል። ሁሉም ነገር የጌታ ቢሆንም፣ጌታ የሁሉም ቤተሰብ በኩር ለራሱ እንደሆነ ተናግሯል።

 

ስለ በኩር ልጅ ልንገነዘበው የሚገባን ሌላው አስፈላጊ ዝርዝር የአባቱን ንብረት ሁለት እጥፍ እንደሚወርስ ነው።

በኦሪት ዘዳግም ምዕራፍ 21 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የሙሴን ሕግ ተመልከቱ፡

 

15 ለአንድ ሰው አንዲቱ የተወደደች አንዲቱም የተጠላች ሁለት ሚስቶች ቢኖሩት፥ ለእርሱም የተወደደችው ደግሞም የተጠላችው ልጆችን ቢወልዱ፥ በኵሩም ከተጠላችው ሚስት የተወለደው ልጅ ቢሆን፥16 ለልጆቹ ከብቱን በሚያወርስበት ቀን ከተጠላችው ሚስት በተወለደው በበኵሩ ፊት ከተወደደችው ሚስት የተወለደውን ልጅ በኵር ያደርገው ዘንድ አይገባውም፤17 ነገር ግን ከከብቱ ሁለት እጥፍ ለእርሱ በመስጠት ከተጠላችው ሚስት የተወለደው ልጅ በኵር እንደ ሆነ ያስታውቅ። የኃይሉ መጀመሪያ ነውና በኵርነቱ የእርሱ ነው። (ዘዳግም 21)

 

ይህ ሁለት እጥፍ ከበኩር ልጅ አይወሰድም ነበር። የበኩር ልጅ ስለሆነ እና ይህን የአባቱን ርስት ሁለት አጥፍ ድርሻ ስለተሰጠው ሊከበር ይገባዋል።

 

በብሉይ ኪዳን የአይሁድ ባህል መሠረት በኩር ልጆች ልዩ ቦታ እንደሚኖራቸው እዚህ እንመለከታለን። የበኩር ልጅ እንደመሆኑ መጠን በአባቱ ፊት ልዩ ርስት እና ግዴታ ይኖረዋል። ይህ ባህላዊ ግንዛቤ ሴት በአገልግሎት ውስጥ የሚኖራትን ሚና በተመለከተ በሐዋርያት ትምህርት ላይ ተጽዕኖ ነበረው። ጳውሎስ ይህንን ለጢሞቴዎስ በነገረበት 1 ጢሞቴዎስ 21213 ላይ ሴቲቱ በዝግታ መማር አለባት፤ምክንያቱም ወንድ አስቀድሞ ተፈጥሮአልና ይላል። ይህን ክፍል በኋላ እንመለከታለን። ለአሁኑ፣ ይህ እንግዲህ ስለ በኩር ልጅ እና ጥቅሞቹ የነበረው ባሕላዊ ግንዛቤ በኋላ ሐዋርያት ሴቶች በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ስላላቸው ሚና ለማስተማር እንደተጠቀሙበት አስተውሉ።

 

 

አሁን ወደ ዘፍጥረት 218 ሄደን እናነባለን፤

 

18 እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት።

ዘፍጥረት 2)

 

እግዚአብሔር ሔዋንን የፈጠረው በኩር ለሆነው አዳም ረዳት ትሆን ዘንድ ነው። አዳም በኩር እንደመሆኑ መጠን ጌታ የሰጠውን ምድር የመንከባከብ ትልቅ ኃላፊነት ነበረበት። ሆኖም ይህንን ብቻውን ማድረግ አልቻለም። የፍጥረት በኩር ሆኖ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት እንዲረዳው የሴቲቱ እርዳታ ያስፈልገው ነበር። እንደ ረዳት ሴቲቱ ዝቅ ያለች አልነበረችም። የረዳትነት ድርሻዋ ቢሆንም እሷም በእግዚአብሔር አምሳል ስለተፈጠረች ከአዳም ጋር በእግዚአብሔር ፊት በነበራት ክብር እኩል ነበረች። እንደ በኩር ልጅ እና ረዳት በመሆን በፍጥረት ላይ ይገዙ ነበር።

 

በዘፍጥረት ኃጢአት ወደ ዓለም ከመግባቱ በፊትም ቢሆን የሥራና የማዕረግ ልዩነት እንደነበር እንመለከታለን። ወንድና ሴት ሆነው በእግዚአብሔር መልክ ተፈጥረዋል፣ ነገር ግን በአንድ ጊዜ ወይም በአንድ መንገድ የተፈጠሩ አልነበረም። አዳም ቀድሞ ሲፈጠር ከዚያም ሔዋን ትከተላለች። አዳም የተፈጠረው ከምድር አፈር ሲሆን ሔዋን ደግሞ ከአዳም አጥንት ተፈጥራለች። አዳም የተፈጠረው በኩር ሆኖ ነው። ሄዋን የተፈጠረችው ረዳት ሆና ነው። ይህ የእግዚአብሔር ሃሳብ ፍጹም በሆነ ዓለም ውስጥ ነበር።

 

አዳምና ሔዋን የኖሩበት ዓለም ፍጹም ሆኖ አልቀረም። እነዚህ የመጀመሪያዎቹ ጥንዶች በኃጢአት ወደቁ። ዘፍጥረት 3 ሰይጣን ሴቲቱን እንዴት እንዳሳታትና እግዚአብሔር ከከለከለው ዛፍ እንድትበላ ያደረጋትን ታሪክ ይተርክልናል። እርስዋም የተከለከለውን ፍሬ የበላችው ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለባሏም ሰጠችው። እግዚአብሔር አዳም የተከለከለውን ፍሬ ከበላ በኋላ የተናገረውን አድምጡ፡

 

17 አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ (ዘፍጥረት 3)

 

እግዚአብሔር አምላክ ምድርን ረገማት፣ አዳምም የሚስቱን ቃል ሰምቷልና ማረስ ነበረበት። እዚህ ላነሳቸው የምፈልጋቸው ሁለት ነጥቦች አሉ።

 

በመጀመሪያ፣ እግዚአብሔር የዚህ ትንሽ ቤተሰብ በኩር እና መንፈሳዊ ራስ ሆኖ አዳምን ይጠብቀው እንደነበረ እንመለከታለን። ቤተሰቡን የመንከባከብ እና የመጠበቅ መንፈሳዊ ግዴታ ነበረበት። መሪ መሆን የብቸኝነት ቦታ ነው። አንዳንድ ጊዜም ተወዳጅ ያልሆኑ ውሳኔዎችን መወሰን ማለት ነው። ጥሩ መሪዎች በእነሱ ስር ያሉትን ሰዎች አስተያየት ቢሰሙም የመጨረሻውን ውሳኔ ለድርጅታቸው፣ለቤተክርስቲያናቸው ወይም ለቤተሰባቸው ይጠቅማል ብለው በሚሰማቸው መንገድ በመመሥረት መወሰን አለባቸው። ይህ ብዙውን ጊዜ በሌሎች የተጠቆሙትን ሃሳቦች ይቃረን ይሆናል።

 

ሁለተኛ፤ከእግዚአብሔር የተሰጠው ትዕዛዝ ቢኖረውም፤አዳም የሚስቱን ቃል ሰምቶ ፍሬውን በልቷል። በዘፍጥረት 317 ላይ ያለው የእግዚአብሔር ክስ የሚያሳየን አዳም የቤተሰቡ ራስ ሆኖ ለዚያ ቤተሰብ የሚበጀውን መንፈሳዊ ጥቅም እንዲጠብቅ እግዚአብሔር ይጠብቅ ነበር። እንደ መሪ እና መንፈሳዊ ራስነት ያለውን ግዴታ አልተወጣም። በምትኩ ሚስቱን በኃጢአት በመተባበር ይህን ውሳኔ አሳልፎ መስጠትን መረጠ።

 

የዘፍጥረት 317 አስፈላጊነት ስለ አዳም ራስነት ማሳየት ብቻ ሳይሆን ጳውሎስ 1 ጢሞቴዎስ 214-15 ላይ ሴት ቤተክርስቲያን ውስጥ በወንድ ላይ ሥልጣን የማይኖራትን ምክንያት ለማሳየትም ተጠቅሞበታል። ይህንን በኋላ እንመለከታለን፤አሁን ግን ነጥቡ ይህ የፍጥረት ታሪክ በአዲስ ኪዳን ጸሓፊዎች ዘንድ የሴቶች በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ያላቸውን ሚና ለመገንዘብ መሠረት ሆኖ መታየቱ ነው።

 

በዘፍጥረት 317 ላይ እግዚአብሔር በሰው ላይ የሰጠውን ተግሣጽ አይተናል። የተከለከለውን ፍሬ ከበላ በኋላ እግዚአብሔር ለሴቲቱ ምን እንደሚላት እናዳምጥ።

 

ለሴቲቱም አለ፦ በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል። (ዘፍጥረት 3)

 

ባለመታዘዟ ምክንያት ሴቲቱ ልጆቿን የምትወልደው በታላቅ ሥቃይ ነው።ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናልየሚለውን ሐረግ አስተውሉ። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ምን እየተከናወነ እንዳለ ተመልከቱ። እግዚአብሔር ሴትን ረዳት ትሆነው ዘንድ ፈጠረ። በኃጢአት መግባት ምክንያት የእርሷ እርዳታ ወደተጻራሪ ምኞትተለውጧል። እግዚአብሔር ወንድን የበኩር ራስ አድርጎ ፈጠረው። ኃጢአት በገባ ጊዜ ይህ ራስነት ወደመግዛትተለወጠ። የኃጢአት መግባት እግዚአብሔር ለወንዶች እና ሴቶች የሰጠውን ሚና አልለወጠም፣ ነገር ግን እነዚያ ሚናዎች እንዴት ጥቅም ላይ ይውላሉ በሚለው ላይ ለውጥ አድርጓል። የራስነት ሥልጣኑን ኃጢአተኛ መሪ ሆኖ ይጠቀማል። እሷም ኃጢአተኛ ረዳት ሆና ከጎኑ ትቆማለች። እግዚአብሔር የበኩር ልጅ እንዲሆን የሰጠውን ኃላፊነት በወንዱ የተዛባ ግንዛቤ በሚያስከትለው መዘዞች ምክንያት ትሠቃያለች። በረዳቱ ሕይወት ውስጥ የመጣው ኃጢአት ባስከተለው ራስ ወዳድነት፣ኩራት እና አመጽ ምክንያት የሚከተለውን ውጤቶች ሁሉ ይለማመዳል።

 

 

ለምልከታ፡

 

ሁለቱም ወንድና ሴት በእግዚአብሔር አምሳል ስለመፈጠራቸው የሚያሳይ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የሰፈረ ምን ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ አለን? ሁለቱም በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠራቸው ምን አንድምታ አለው?

ኦሪት ዘፍጥረት እንደሚነግረን እግዚአብሔር ወንዱን እና ሴቲቱን እርሱ በፈጠራቸው እንስሳትና በምድር ሁሉ ላይ ስልጣንን ሰጣቸው። ይህ ለወንዱ እና ሴቲቱ ያለው አንድምታ ምንድን ነው?

እግዚአብሔር የሰጣቸውን ኃላፊነት ይወጡ ዘንድ ወንድና ሴትን አንዱ ለአንዱ አስፈላጊ ይሆኑ ዘንድ የተለያዩ አድርጎ ፈጠራቸው። በዚህ ተግባር ውስጥ እንደ ወንድና ሴት ያለን ልዩነት እርስ በርስ የሚደጋገፈው እንዴት ነው? እርስ በእርሳችን የምናስፈልገው ለምንድ ነው?

ሴት ከምድር አፈር ሳይሆን ከወንድ መፈጠሯ ምን ትርጉም አለው? ይህ በዚያ ዘመን እግዚአብሔር ለሰው ካቀረባቸው እንስሳት የሚለያት እንዴት ነው? ዛሬ ሴቶችን የምንይዝበትን መንገድ በተመለከተ ይህ ለእኛ ምን አንድምታ አለው?

አዳም መጀመሪያ መፈጠሩ አስፈላጊ የሆነው ለምንድ ነው?

እግዚአብሔር ሔዋንን ረዳት አድርጎ ፈጠረ? ይህ ከአዳም ጋር ባላት ግንኙነት ምን አንድምታ ነበረው?

እግዚአብሔር ከውድቀት በኋላ በአዳም ላይ ያደረገው ውግዘት እሱን መንፈሳዊ ራስ አድርጎ እንደጠብቀው የሚያሳየን እንዴት ነው?

ኃጢአት እግዚአብሔር በገነት ውስጥ ለወንዶች እና ለሴቶች በሰጣቸው ሚናዎች ላይ ምን ተጽዕኖ አሳደረ?


ለጸሎት፡

 

ወንድና ሴት አድርጎ የፈጠረንን ጌታ ለማመስገን ትንሽ ጊዜ ውሰዱ። ያንን ምስል እንድትመለከቱ እና ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ይህን ምስል በተለያዩ መንገዶች እንዴት እንደሚያንጸባርቁ እንዲረዳችሁ ጠይቁት።

የሃብቱ አስተዳዳሪዎች አድርጎ ምድርን እንንከባከብ ዘንድ የሰጠንን ኃላፊነት እንድንወጣ እንደ ወንድና ሴት እግዚአብሔር ይረዳን ዘንድ ጠይቁ። በዚህ ውስጥ እንዴት የበለጠ ታማኝ መሆን እንደምትችሉ ጠይቁ።  

ወንድና ሴት አድርጎ ስለፈጠረን ጌታን ለማመስገን ትንሽ ጊዜ ውሰዱ። እንደ ዓላማው በጋራ ተስማምተን የምንሰራበትን መንገድ እንድንፈልግ እንዲረዳን ጠይቁ።

በየዕለቱ ተጽዕኖ የሚያደርግብን ኃጢአት ቢኖርም የተፈጠርንበትን ኃላፊነት እንወጣ ዘንድ እንዲረዳን እግዚአብሔርን ጠይቁ። ወንድ ወይም ሴት ሆናችሁ ለተፈጠራችሁበት ዓላማ ታማኝ ላልሆናችሁባቸው ጊዜያት ይቅር እንዲላችሁ ጠይቁ።


 

ምዕራፍ 2 – የብሉይ ኪዳን አምልኮ

እግዚአብሔር ምድርን ይገዙ ዘንድ ወንድና ሴትን አድርጎ በአምሳሉ እንደፈጠራቸው በዘፍጥረት ላይ ካለው የፍጥረት ምንባብ ተምረናል። ሁለቱም ወንድና ሴት በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ ቢሆንም፣ ዳሩ ግን የተፈጠሩት ልዩ እና የተለየ ሚና ያላቸው ሆነው ነው። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ እነዚህ ልዩነቶች በብሉይ ኪዳን አምልኮ ውስጥ እንዴት እንደሠሩ እንመልከት።

 

ሴቶች እና ወንዶች በጋራ ያመልኩ ነበር

 

በዘጸአት 14 ላይ እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ ከወጡ በኋላ ያሳድዳቸው ዘንድ ፈርዖን ሰራዊቱን ወደ ምድረ በዳ ላካቸው። እግዚአብሔር ልጆቹ እንዲሻገሩ የቀይ ባህርን ውሃ ከፈለላቸው። ግብፃውያን በተከተሏቸው ጊዜ እግዚአብሔር እንደ ግድግዳ የቆመውን ውኃ በላያቸው ላይ መለሰው።

 

በሌላ በኩል ደግሞ፣ሙሴ ሕዝቡን በምስጋና እና በአምልኮ መዝሙር ይመራ ነበር፡-

 

1 በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩ፦ በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና

ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ።

2 ጕልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነውማለሁ፥ የአባቴ አምላክ ነው ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ፡፡

3 እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው፥ (ዘጸአት 15)

 

ሙሴ በዚህ የምስጋና መዝሙር ሕዝቡን ከመራ በኋላ ማርያም በእጇ ከበሮ ይዛ ሴቶቹን በበዓል ጭፈራ ትመራ ነበር።

 

20 የአሮን እኅት ነቢይቱ ማሪያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዘፈን በኋላዋ ወጡ።

21 ማርያምም እየዘመረች መለሰችላቸው። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። (ዘጸአት 15)

 

ይህ ጭፍራ እስራኤልን ከግብፅ ጦር ካዳነ በኋላ ለእግዚአብሔር የቀረበ አምልኮ አካል ነበር። በዚህ በዓል ላይ ማርያምና ሴቲቱ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

 

1 ሳሙኤል 1867 ላይ ተመሳሳይ ክስተት እንመለከታለን። ዳዊት ፍልስጤማውያንን ድል አድርጎ ወደ ቤቱ ገና መመለሱ ነው። ወደ እየሩሳሌም ከተማ ሲገባ ሴቶቹ ወደ እርሱ ወጡ። ከጠላቶቻቸው ያዳናቸውን የእግዚአብሔርን ቸርነት ለማክበር ይዘምሩ እና ይጨፍሩ ነበር።

 

6 እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ፥ እየዘመሩና እየዘፈኑ እልልም እያሉ ከበሮና አታሞ ይዘው ንጉሡን ሳኦልን ሊቀበሉ ሴቶች ከእስራኤል ከተሞች ሁሉ ወጡ።

7 ሴቶችም፦ ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም እልፍ ገደለ እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር። (1 ሳሙኤል 18)

 

2 ዜና 3525 ላይ ሴቶች እና ወንዶች በጌታ እግዚአብሔር አምልኮ ሆነው የለቅሶን መዝሙር ይዘምሩ እንደነበር እንማራለን፡፡

 

25 ኤርምያስም ለኢዮስያስ የልቅሶ ግጥም ገጠመለት፤ እስከ ዛሬም ድረስ ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ሁሉ በልቅሶ ግጥማቸው ስለ ኢዮስያስ ይናገሩ ነበር፤ ይህም በእስራኤል ዘንድ ወግ ሆኖ በልቅሶ ግጥም ተጽፎአል። (2 ዜና 35)

 

በዕዝራ ዘመን ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱት ቡድኖች መካከል 200 ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ነበሩ (ዕዝራ 265 ተመልከቱ)

 

በመሳፍንት 51 ላይ ንጉስ የአቢኒኤም ድል ካደረጉ በኋላ ነቢይት ዲቦራ እና የጦር አዛዡ ባርቅ እንዴት ለጌታ የምስጋና መዝሙር እንደዘመሩ እንመለከታለን።

 

የብሉይ ኪዳን ሴቶች ከወንዶች ጋር በነፃነት ማምለክ ይችሉ ነበር። እግዚአብሔርን እና ታላቅ ድሎችን ለማክበር ይዘመሩ እንዲሁም ያሸበሽቡ ነበር።

 

 

ወንዶች እና ሴቶች ቃሉን በመስበክ እና በማንበብ በአንድነት ይሆኑ ነበር

 

በብሉይ ኪዳን ሴቶች ከወንዶች ጋር መቀላቀል ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል ሲነበብና ሲታወጅም አብረው ይሆኑ ነበር። በዘዳግም 3112-13 ሙሴ የእግዚአብሔር ሕግ ሲነበብ እንዲሰሙ የወንዶችን፣ የሴቶችን እና የሕጻናትን ጉባኤን አዝዞ ነበር፡

 

 

12 ይሰሙና ይማሩ ዘንድ፥ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ይፈሩ ዘንድ፥ የዚህንም ሕግ ቃሎች ሁሉ ጠብቀው ያደርጉ ዘንድ ሕዝቡን ወንዶችንና ሴቶችን ሕፃናቶችንም በአገራችሁ ደጅ ያለውንም መጻተኛ ሰብስብ።

13 የሕግ ቃላት የማያውቁ ልጆቻቸውም ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ልትወርሱአት በምትሄዱባት ምድር በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ ይስሙ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርንም መፍራት ይማሩ። (ዘዳግም 31)

 

ወንዶች፣ ሴቶች እና ህጻናት ቃሉን በማንበብ እሱን እና ዓላማውን እንዴት መከተል እንደሚችሉ ይማሩ ዘንድ የእግዚአብሔር ዓላማ ነበር።

 

ኢያሱ 8 ላይ እስራኤል በጋይ ከተሸነፉ በኋላ፣ ኢያሱ ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን ያድሱ ዘንድ ህዝቡን ሰበሰበ። የሕጉንም ቃል አነበበላቸው። የዚህን ሕግ ቃል ለመስማት ወንዶችና ሴቶች ተሰበሰቡ፡

 

34 ከዚህም በኋላ በሕጉ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ሁሉ፥ የሕጉን ቃሎች ሁሉበረከቱንና እርግማኑን አነበበ።

35 ኢያሱም በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ በሴቶቹም በሕፃናቱም በመካከላቸውም በሚኖሩት መጻተኞች ፊት ሁሉን አነበበ እንጂ ሙሴ ካዘዘው አንዲት ቃል አላስቀረም።(ኢያሱ 8)

 

ካህኑ ዕዝራም የሕጉን መጽሐፍ ቃል ይሰሙ ዘንድ ወንዶችና ሴቶች በፊቱ ተሰበሰቡ።

 

1 ሰባተኛውም ወር በደረሰ ጊዜ የእስራኤል ልጆች በከተሞቻቸው ነበሩ። ሕዝቡም ሁሉ በውኃው በር ፊት ወዳለው አደባባይ እንደ አንድ ሰው ሆነው ተሰበሰቡ፤ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ያዘዘውን የሙሴን ሕግ መጽሐፍ ያመጣ ዘንድ ጸሐፊውን ዕዝራን ተናገሩት።

2 ካህኑም ዕዝራ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ሕጉን በማኅበሩ በወንዶችና በሴቶች አስተውለውም በሚሰሙት ሁሉ ፊት አመጣው።

3 በውኃውም በር ፊት ባለው አደባባይ ላይ ቆሞ፥ ወንዶችና ሴቶች የሚያስተውሉም ሲሰሙ፥ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ቀትር ድረስ አነበበው የሕዝቡም ሁሉ ጆሮ የሕጉን መጽሐፍ ለመስማት ያደምጥ ነበር። (ነህምያ 8)

 

ነህምያ 8 የሕጉ ቃሎች በሚነበቡበት ጊዜ ሌዋውያን የእነዚህን ቃላት ትርጉም ሕዝቡን እንዳስተማሩ በመናገር ይቀጥላል። ዐውደ-ጽሑፉ በግልጽ እንደሚያሳየው በዚያ ቀን ወንዶችና ሴቶች በጉባኤ ውስጥ ነበሩ። ሴቶች የእግዚአብሔርን ቃል በማንበብ እና በመስበክ ከወንዶች ጋር ይሰበሰቡ ነበር።

 

ሴቶችና እና ወንዶች በአደባባይ ሐጢአታቸውን ይናዘዙ ነበር

 

በብሉይ ኪዳን ሴቶች እና ወንዶች በአደባባይ ኃጢአታቸውን መናዘዝ እና ስለ ኃጢአታቸውም ያለቀሱበት ቢያንስ ሁለት አጋጣሚዎች አሉ። እንግዲህ በነህምያ 8 በጠቀስነው ምንባብ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የጌታን ቃል ለመስማት እንደተሰበሰቡ እንመለከታለን። በዚያ ቀን ለእግዚአብሔር ቃል ስብከትና ትምህርትሕዝቡ ሁሉየሰጡትን ምላሽ ተመልከቱ፡-

 

9 ሐቴርሰታ ነህምያም ጸሐፊውም ካህኑ ዕዝራ ሕዝቡንም የሚያስተምሩ ሌዋውያን ሕዝቡን ሁሉ፦ ዛሬ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ቀን ነው፤ አታልቅሱ እንባም አታፍስሱ አሉአቸው፤ ሕዝቡ ሁሉ የሕጉን ቃል በሰሙ ጊዜ ያለቅሱ ነበርና። (ነህምያ 8)

 

ሕዝቡ ሁሉየሕጉን ቃል በሰሙ ጊዜ አለቀሱ። እነዚህ ሰዎች፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች፣በቃሉ እውነት ተነክተው ነበር። ወንዶችና ሴቶች በአንድነት በእግዚአብሔር ላይ በፈጸሙት ኃጢአት አዝነው ነበር።

 

ዕዝራ 101 ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል፤

 

1 ዕዝራም እያለቀሰና በእግዚአብሔር ቤት ፊት እየወደቀ በጸለየና በተናዘዘ ጊዜ ከእስራኤል ዘንድ የወንድና የሴት የሕፃናትም እጅግ ታላቅ ጉባኤ ወደ እርሱ ተሰበሰበ፤ ሕዝቡም እጅግ አለቀሱ። (ዕዝራ 10)

 

ወንዶችም ሴቶችም በእግዚአብሔር መንፈስ ተነክተው ነበር። በአንድነት ኃጢአታቸውን ተናዘዙ በእግዚአብሔርም ፊት አዘኑ።

 

ወንዶች እና ሴቶች ለጌታ መስዋዕትን ያመጡ ነበር

 

ሴቶች ልክ እንደ ወንዶች መባዎቻቸውን ለጌታ እንዲያቀርቡ ይበረታቱ ነበር።

 

20 የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከሙሴ ፊት ወጡ።

21 ከእነርሱም ሰው ሁሉ ልቡ እንዳነሣሣው መንፈሱም እሺ እንዳሰኘው ለመገናኛው ድንኳን ሥራ ለማገልገያውም ሁሉ ለተቀደሰውም ልብስ ለእግዚአብሔር ስጦታ አመጡ።              

22 ወንዶችና ሴቶችም ልባቸው እንደ ፈቀደ ማርዳዎችን፥ ሎቲዎችንም፥ ቀለበቶችንም፥ ድሪዎችንም፥ የወርቅ ጌጦችንም ሁሉ አመጡ፤ ሰዎችም ሁሉ የወርቅ ስጦታ ወደ እግዚአብሔር አቀረቡ። (ዘጸአት 35)

 

29 ከእስራኤል ልጆችም ያመጡ ዘንድ ልባቸው ያስነሣቸው ወንዶችና ሴቶች ሁሉ ሙሴ ይሠራ ዘንድ እግዚአብሔር ላዘዘው ሥራ ሁሉ ለእግዚአብሔር ስጦታ በፈቃዳቸው አመጡ።       (ዘጸአት 35)

 

እግዚአብሔር ወንድ በሚያቀርበው እና ሴት በምታቀርበው መባ መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም። ልባቸው ያነሳሳቸው ሁሉ መባዎቻቸውን ለጌታ ለማቅረብ ነፃ ነበሩ።

  

ወንዶች እና ሴቶች ለጌታ ቃል ኪዳን ይገቡ ነበር

 

በዘኍልቍ 6:1-4 ላይ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እንደ ናዝራዊ ለጌታ ልዩ የሆነ የመለየት ቃል ኪዳን ሊያደርጉ እንደቻሉ እናነባለን።

 

2 ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው፦ ሰው ወይም ሴት ለእግዚአብሔር ራሱን የተለየ ያደርግ ዘንድ የናዝራዊነት ስእለት ቢሳል፥

3 ከወይን ጠጅና ከሚያሰክር መጠጥ ራሱን የተለየ ያድርግ፤ ከወይን ወይም ከሌላ ነገር የሚገኘውን ሆምጣጤ አይጠጣ፥ የወይንም ጭማቂ አይጠጣ፤ የወይን እሸት ወይም ዘቢብ አይብላ።

4 ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ከወይን የሆነውን ነገር ሁሉ ከውስጡ ፍሬ ጀምሮ እስከ ገፈፎው ድረስ አይብላ። (በዘኍልቍ 6)

 

የናዝራዊነት ቃል ኪዳን ለተወሰነ ጊዜ እና ለአንድ ዓላማ ለጌታ የመለየት ልዩ ስለት ነበር። በዘኍልቍ 62 ላይ ይህ አንድ ወንድ ወይም ሴት ሊገቡት የሚችሉት የመለየት ቃል ኪዳን እንደሆነ ግልጽ ነው። በዚህ ስለት ላይ የተደረገ ምንም ልዩነት የለም።

 

ሴቶች ለጌታ ስለት መግባት ቢችሉም፣ሴቶች ስለት በሚፈጽሙበት ጊዜ አንዳንድ ገደቦች እንዳሉ በዘኁልቁ 30 ላይ እናነባለን። የሙሴ ሕግ ከወላጆቿ ጋር በቤት ውስጥ የምትኖር አንዲት ሴት አባቷ የማይቀበለው ከሆነ የገባችው ስለት ሊሻር እንደሚችል ይገልጻል፡

 

 

3 ሴትም ደግሞ ለእግዚአብሔር ስእለት ብትሳል፥ እርስዋም በአባትዋ ቤት ሳለች በብላቴንነትዋ ጊዜ ራስዋን በመሐላ ብታስር፥

4 አባትዋም ራስዋን ያሰረችበትን መሐላ ስእለትዋንም ቢሰማ፥ አባትዋም ዝም ቢላት፥ ስእለትዋ ሁሉ ይጸናል፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል።

5 አባትዋ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ ስእለትዋ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላዋ አይጸኑም፤ አባትዋ ከልክሎአታልና እግዚአብሔር ይቅር ይላታል።(ዘኁልቁ 30)

 

ባል ላላት ሴትም ተመሳሳይ መመሪያ ተግባራዊ ይሆናል። ባሏ የቤቱ አስተዳዳሪ እንደመሆኑ መጠን ሚስቱ የገባችውን ስለት የማይቀበል ከሆነ ስለቱን መሻር ይችላል፡

 

6 በተሳለችም ጊዜ ራስዋንም በመሐላ ያሰረችበት ነገር ከአፍዋ በወጣ ጊዜ ባል ያገባች ብትሆን፥

7 ባልዋም ቢሰማ፥ በሰማበትም ቀን ዝም ቢላት፥ ስእለትዋ ይጸናል፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ይጸናል።

8 ባልዋ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ በእርስዋ ላይ ያለውን ስእለትዋን ራስዋንም በመሐላ ያሰረችበትን የአፍዋን ነገር ከንቱ ያደርገዋል፤ እግዚአብሔርም ይቅር ይላታል። (ዘኁልቁ 30)

 

ለጌታ ስለት መሳልን በተመለከተ፤ሴቲቱ ነጻ ሆና ሳለ ያላገባች ወይም ያገባች ሴት የቤተሰቧ አለቃን ይሁንታ ማግኘት ይኖርባታል።

 

 

በመንፈሳዊ ጉዳዮች ወንዶችን መምከር

 

በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ ሴቶች በእግዚአብሔር ፊት ኃላፊነታቸውን ያልወጡትን ወንዶች ለመምከር ጌታ ተጠቅሞባቸዋል። በዘጸአት 424-26 ጌታ ሙሴን ሊገድለው እንዴት እንደፈለገ እናነባለን። ሚስቱ ሲፓራም ባልጩት ወሰደች፥የልጅዋንም ሸለፈት ገረዘች፥ ወደ እግሩም ጣለችው፤የእግዚአብሔርን ቁጣ በማረጋጋት የባሏን ህይወት አዳነች። ሙሴ የቤተሰቡ መንፈሳዊ ራስ ሆኖ ሳለ ልጃቸውን ባለመገረዝ ኃላፊነቱን መወጣት አልቻለም። ሚስቱምአንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህበማለት ገሠጸችው (ዘጸአት 425) እንግዲህ እሷ እርምጃ ወስዳ ባይሆን ኖሮ ሙሴ ግብፅ ላይደርስ ይችል ነበር። ሙሴ ግዴታውን ሳይወጣ ሲቀር እሷም የእሱን ኃላፊነት ወስዳ ቤተሰቡን አትርፋለች። ይህ ኃላፊነት የቤተሰቡ ራስ የሆነው የወንዱ ቢሆንም፣ በዚህ ጉዳይ ላይ፣ ሲፓራ፣ እንደ ሚስት የወሰደችው ባሏ እንደሚገባው መሪ መሆን ባለመቻሉ ነው።

 

ዲቦራ ባርቅን እንዲበረታ እና ጠላታቸውን የሆነውን ሲሣራንና ሠራዊቱን እንዲዋጋ መከረችው። ባርቅ ይህን ኃላፊነት ለመሸከም የፈራ ይመስላል። ዲቦራ ግን ለጌታ ትዕዛዝ ታማኝ እንዲሆን እና እንደ ወታደራዊ አዛዥ የነበረበትን ኃላፊነት እንዲወጣ አደረገችው።

 

6 ልካም ከቃዴስ ንፍታሌም የአቢኒኤምን ልጅ ባርቅን ጠርታ፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፦ ሄደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጣ፥ ከአንተም ጋር ከንፍታሌምና ከዛብሎን ልጆች አሥር ሺህ ሰዎች ውሰድ፤ (መሣፍንት 4)

 

ባርቅ ከሲሣራ ጋር ለመዋጋት የሚስማማው ዲቦራ አብራው ከሄደች ብቻ ነው።

 

8 ባርቅም፦ አንቺ ከእኔ ጋር ብትሄጂ እኔ እሄዳለሁ፤ አንቺ ግን ከእኔ ጋር ባትሄጂ እኔ አልሄድም አላት።

9 እርስዋም፦ በእውነት ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሲሣራን በሴት እጅ አሳልፎ ይሰጣልና በዚህ በምትሄድበት መንገድ ለአንተ ክብር አይሆንም አለችው። ዲቦራም ተነሥታ ከባርቅ ጋር ወደ ቃዴስ ሄደች።           (መሣፍንት 4)

 

 

በጌታ ስላልታመነ እና ይህንን ኃላፊነት በፈቃዱ ስላልወሰደ፣ባርቅ ሲሣራን የሚያሸንፈው አይሆንም። ይልቁንም የሔቤር ሚስት ኢያዔል ለዕረፍት እና ለመዝናናት ወደ ድንኳኗ በመጣ ጊዜ ይህን ታላቅ የጦር አዛዥ ገደለችው (መሳፍንት 417-22 ተመልከት) የዲቦራ ምክር ባይሆን ኖሮ ሲሣራ ምድሪቱን አበላሽቶ ሊሆን ይችል ነበር። እግዚአብሔር የጠራው መሪ እንዲሆን ባርቅን መሞገት አስፈልጓት ነበር። እነዚህ ሴቶች የሃገራቸውን እና የቤተሰቦቻቸው ወንድ እግዚአብሔር የጠራቸው አይነት መሪ እንዲሆኑ በመሞገት ረገድ ወሳኝ ሚና ነበራቸው።

 

 

ሴቶች በመገናኛው ድንኳን ያገለግሉ ነበር

 

ሴቶች በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አገልግሎት ነበራቸው። በዚህ የመገናኛ ድንኳን ደጃፍ ላይ ስለ አገልግሎታቸው የሚናገር ማስረጃዎች አሉን። ለምሳሌ ባስልኤል በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ውስጥ ከሚያገለግሉት ከሴቶች መስታወት ለድንኳኑ የሚውለውን የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫው እንዴት እንደሠራ እናነባለን፡

 

8 የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉ ከሴቶች መስተዋት ከናስ አደረገ።          (ዘጸአት 38)

 

ካህኑ ዔሊ በክህነት የሚያገለግሉ ልጆች ነበሩት። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን የማያውቁ ምናምነቴዎች ብሎ ይገልጻቸዋል (1ሳሙ 212) ከአስጸያፊ ኃጢአታቸው አንዱ 1 ሳሙኤል 222 ላይ ተገልጿል፡

 

22 ዔሊም እጅግ አረጀ፤ ልጆቹም በእስራኤል ሁሉ ላይ ያደረጉትን ሁሉ፥ በመገናኛውም ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር እንደ ተኙ ሰማ። (1 ሳሙኤል 2)

 

የዔሊም ልጆች በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር ተኙ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እነዚህ ሴቶች በማደሪያው ድንኳን ደጃፍ ላይ ለዝሙት አዳሪነት የተገኙ አልነበሩም፤ ይህ ካልሆነ ግን የሙሴን ሕግ የሚጻረር በመሆኑ ፈጥነው ይወገዱ ነበር። ዘጸአት 388 እነርሱ እያደረጉ የነበሩትን ነገርአገልግሎትበማለት ይገልጻል። 1 ሳሙኤል 2:12 “አገልግሎትሲል ያብራራዋል።

 

እነዚህ ሴቶች በማደሪያው ድንኳን ደጃፍ ላይ ስለሚያደርጉት አገልግሎት ትክክለኛ ምንነት እርግጠኛ ባንሆንም በጽዳት ወይም በበር ጠባቂነት የማገልገል ሚና እንደነበራቸው ይታሰባል። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ዓመቱን ሙሉ ለሚከበሩ ልዩ በዓላት በመዘመር እና በማሸብሸብ ሲሳተፉ እንደነበር ያመለክታሉ። ተግባራቸው ምንም ይሁን ምን፣ የማደሪያው ድንኳን አጠቃላይ አገልግሎት አስፈላጊ ክፍል ነበር።

 

ሴቶች በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ከነበራቸው ተግባር ባሻገር በብሉይ ኪዳን ሃይማኖታዊ ሕይወት ውስጥ ሌሎች የአገልግሎት ሚናዎችን ተጫውተዋል። በዘፀአት 352526 ላይ ለማደሪያው ድንኳን ግንባታ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ለመሥራት የፍየል ጠጉር ስለሚፈትሉ ሴቶች እናነባለን።

 

25 በልባቸው ጥበበኞች የሆኑ ሴቶችም በእጃቸው ፈተሉ፥ የፈተሉትንም ሰማያዊውን ሐምራዊውንም ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ አመጡ።

26 ልባቸውም በጥበብ ያስነሣቸው ሴቶች ሁሉ የፍየልን ጠጕር ፈተሉ። (ዘጸአት 35)

 

እነዚህ ሴቶች በዘፀአት 3525 ላይ እንደጥበበኛ ሴቶችተገልጸዋል። ይሁን እንጂ ይህ በእነዚህ ሴቶች በኩል የተደረገ የበጎ ፈቃድ ድርጊት መሆኑን አስተውሉ። ቁጥር 26 ይህን ጉልህ አስተዋጽዖ ያደረጉት ችሎታቸውን ለመጠቀም ልባቸው ያነሳሳቸው እንደነበሩ ይነግረናል። እነርሱ በችሎታቸው፣በበጎ ልባቸው እና በለጋስነታቸው ይታወቃሉ።

 

በመስተንግዶ አገልግሎት የብሉይ ኪዳን ሴቶችም ጉልህ ሚና ተጫውተዋል። ጌታ በሰራፕታ ያለች አንዲት ባልቴት የአገልጋዩን የኤልያስን ፍላጎት እንድታሟላ እንዳዘዛት ይናገራል።

 

8 ተነሥተህም በሲዶና አጠገብ ወዳለችው ወደ ሰራፕታ ሂድ፥ በዚያም ተቀመጥ፤9 እነሆም፥ ትመግብህ ዘንድ አንዲት ባልቴት አዝዣለሁ የሚል የእግዚአብሔር ቃል መጣለት።

                 (1 ነገስት 17)

 

እግዚአብሔር ይህችን ባልቴት ነቢዩን እንድትደግፍ ጠርቶ ቤት ሰጠው። ይህ ለኤልያስ በችግር ጊዜ ታላቅ በረከት ነበር።

 

የኤልያስ ተተኪ የሆነው ኤልሳዕ በሱነም ክልል ሲያገለግል ተመሳሳይ በረከት አግኝቷል። 2 ነገ 4 ላይ የሆነውን ታሪክ አድምጡ፡

 

8 አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ ኤልሳዕ ወደ ሱነም አለፈ፥ በዚያም ታላቅ ሴት ነበረች፤ እንጀራ ይበላ ዘንድ የግድ አለችው፤ በዚያም ባለፈ ቍጥር እንጀራ ሊበላ ወደዚያ ይገባ ነበር።

9 ለባልዋም፦ ይህ በእኛ ዘንድ ሁልጊዜ የሚያልፈው ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆነ አውቃለሁ።

10 ትንሽ ቤት በሰገነቱ ላይ እንሥራ፤ በዚያም አልጋ ጠረጴዛ ወንበርና መቅረዝ እናኑርለት፤ ወደ እኛም ሲመጣ ወደዚያ ይገባል አለችው። (2 ነገስት 4)

 

ይህች ሃብታም ሴት በልግስና ለኤልሳዕ ምግብ የምታቀርብለት ብቻ ሳይሆን ኤልሳዕ በአካባቢው ባለፈ ቁጥር የሚያርፍበት አንድ ትንሽ ክፍል በሰገነታቸው ላይ አልጋ፣ጠረጴዛ፣ ወንበርና ፋኖስ እንዲሰሩለት ለባሏ ነገረችው። ሃብቷን የእግዚአብሔር አገልጋይ ለማገልገል ተጠቀመችበት። ነቢዩ 2 ነገ 413-17 ላይ ለታላቅ ለጋስነቷ በምላሹ ምን ማድረግ እንደሚችል ሲጠይቃት ምን ያህል አመስጋኝ እንደነበረ ፍንጭ እናገኛለን። ሴቲቱ ልጅ አልወለደችም ነበር፣ ነገር ግን ኤልሳዕ ይህን ነገር ለእግዚአብሔር ባቀረበ ጊዜ፣ እርሷ እና ባሏ በልጅ ተባረኩ።

 

1 ሳሙኤል 19-11 የነቢዩ የሳሙኤል እናት ልጅ ታገኝ ዘንድ ለመጸለይ እና ጌታ ልጅ ከሰጣት ለእግዚአብሔር ልትቀድሰው ስለት ልትሳል በመጣችበት ቤተመቅደስ ውስጥ እናገኛታለን። ይህን ሳሙኤልን የተባለውን ልጇን ለእግዚአብሔር ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለማቅረብ በሚቀጥለው ዓመት ትመለሳለች (1 ሳሙ 126-28) ከዚህ የበለጠ መስዋዕትነት መክፈል አልቻለችም። ልጇም ደግሞ የእስራኤል ሕዝብ ከሚያውቁት ታላላቅ ነቢያት አንዱ ይሆናል።

 

እነዚህ ሴቶች ታማኝ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ነበሩ። ችሎታቸውን እና ሃብታቸውን ለጌታ ለመጠቀም ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል። ጊዜያቸው፣ጥረታቸው እና ልግስናቸው መንግሥቱን በመስፋፋት ረገድ በጌታ ዘንድ የተባረከ ነበር።

 

ሴቶች ከእግዚአብሔር ቃል ይቀበሉ ነበር።

 

የሳምሶን እናት በመሳፍንት 13 ላይ አንድ መልአክ ጎበኝቷት ነበር። ይህም መልአክ እስራኤልን ከባርነት ነፃ የሚያወጣ ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ነገራት።

 

የሙሴ እህት ማርያም በዘጸአት 1520-21 ነብይት እንደነበረች ይናገራል። ከበሮዋን ይዛ የነበሩትን ሴቶች በጭፈራና በዝማሬ እየመራች ከግብጽያውያን ያዳናቸውን እግዚአብሔርን ያመሰግኑ እና ያመልኩ ነበር።

 

በመሣፍንት 4 ላይ ተብራርቶ የቀረበልንን የነቢይቱን የዲቦራ አገልግሎት አድምጡ፡

 

 

4 በዚያ ጊዜም ነቢይቱ የለፊዶት ሚስት ዲቦራ በእስራኤል ላይ ትፈርድ ነበረች።

5 እርስዋም በተራራማው በኤፍሬም አገር በራማና በቤቴል መካከል ካለው የዲቦራ ዛፍ ከሚባለው ከዘንባባው በታች ተቀምጣ ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እርስዋ ለፍርድ ይወጡ ነበር። (መሣፍንት 4)

 

የእስራኤል ሕዝብ ለፍርድ ወደ እርስዋ መጡየሚለውን ሐረግ ተመልከቱ። እዚህ ያለው ሐሳብ እነዚህ ሰዎች ችግሮቻቸውን መፍታት እንደሚያስፈልጋቸው እና የጌታ ትምህርት ለእነሱ ምን እንደሆነ ማወቅ ይፈልጉ ነበር። ወደ ዲቦራ በሚመጡ ጊዜ እሷም ስለ እነርሱ ጌታን ታማክረው ነበር።

 

ለረጅም ጊዜ በተወው ቤተመቅደስ ውስጥ የሕጉን መጽሐፍ ካገኘ በኋላ፣ንጉሥ ኢዮስያስ እግዚአብሔርን እንዲጠይቅ ካህኑን ኬልቅያስን አዘዘው (2 ነገስት 221213) ካህኑና አገልጋዮቹ ነቢይቱን ሕልዳናን አግኝተው አማከሯት። ለእነዚህ ሰዎች ከእግዚአብሔርን ዘንድ ቃል ትፈልግ ነበር፤ከዚያም ይህን ቃል ይዘው ወደ ንጉሡ ተመለሱ (2 ነገ 2214-20) በሕልዳና በኩል፣ጌታ እነዚህን ሰዎች ስለሚመጣው ፍርድ ያስታውሳቸዋል።

 

እግዚአብሔር በነቢያቱ በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ በዘመናቸው ለነበሩት ወንድ አመራር ተናገረ። የነቢይነት ስጦታው በወንዶች ላይ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። ወይም ይህ ስጦታ ያላት ሴት ስጦታዋን ለሴቶች ብቻ ትጠቀም ዘንድ የተገደበ አልነበረም።

 

 

ነጻ አውጪ ሴቶች

 

መጽሐፍ ቅዱስ እስራኤላውያንን ከጠላቶቿ ነፃ ያወጡትን የበርካታ ሴቶች ታሪክ ይተርካል። ዲቦራ ባትሆን ኖሮ ባራቅ የሲሣራን ሠራዊት አያሸንፍም ነበር (መሳፍንት 4 ተመልከቱ) ኢያኤል ደግሞ የጦር አዛዡን ሲሣራን ገደለችው፣ እስራኤልንም ከዚህ ጨካኝ ጨቋኝ አድነዋል (መሳፍንት 418-23 ተመልከቱ) ክፉው ንጉሥ አቢሜሌክ ከቴቤዝ ከተማ ቅጥር ላይ ድንጋይ በራሱ ላይ በወረወረችው ሴት ተገደለ (መሳፍንት 950-55 ተመልከት) የአቢግያ ጥበብ የተሞላበት ምክር ዳዊት የናባልን ቤተሰብ በሙሉ እንዳያጠፋ ከለከለው (1 ሳሙኤል 25 ተመልከቱ) እነዚህ ሴቶች በችግር ጊዜ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ታላቅ ድል ለማምጣት እግዚአብሔር ተጠቅሞባቸዋል።

 


ገደቦች

 

እንደተመለከትነው ሴቶች በእስራኤል ሐይማኖታዊ ሕይወት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ በእነሱ ላይ የተወሰኑ ገደቦች ነበሩ። እነዚህ ገደቦች በሁለት ዋና ዋና ርዕሶች ስር ይከፈላሉ።

 

አለመንጻት

 

በብሉይ ኪዳን በሴቶች ላይ የተጣለው የመጀመሪያው የእገዳዎች ስብስብ ከሥርዓታዊ ርኩሰት ጋር የተያያዘ ነው። በትክክል ለመናገር ይህ ገደብ ለወንዶችም ጭምር ነበር።

 

አንድ ወንድ ወይም ሴት ርኩስ ሊሆኑ የሚችሉባቸው ብዙ መንገዶች ነበሩ። ለምሳሌ የሞተን ሰው አስከሬን መንካት አንድን ሰው በእግዚአብሔር ፊት ርኩስ ያደርገዋል፤በዚህም ምክንያት መባቸውን ለእግዚአብሔር እንዲያቀርቡ አይፈቀድላቸውም ነበር (ዘሌዋውያን 96 ተመልከቱ) አንድ ሰው የቆዳ በሽታ እንዳለበት ከታወቀ፣ በካህኑ እንደ ርኩስ ተቆጥሮ ሊታወጅ እና ወደ ማደሪያው ድንኳን እንዳይሄድ ወይም በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል እንኳን እንዳይዘዋወር ሊከለከል ይችላል (ዘሌዋውያን 13 ተመልከቱ) ሌላው የመርከስ ዘዴ ርኩስ የሆነን እንስሳ ወይም ነፍሳት በመንካት ነው (ዘሌዋውያን 1113-40 ተመልከቱ) እነዚህ አጋጣሚዎች አንድ ግለሰብ እስኪነጻ ድረስ ጌታን እንዳያመልክ ሊያደርጉት ይችላሉ።

 

ከላይ ከተጠቀሱት ምሳሌዎች በተጨማሪ ከሰውነት የሚወጡ ጉዳዮች ነበሩ። ለምሳሌ አንድ ሰው ከሰውነቱ ፈሳሽ ቢወጣ እንደ ርኩስ ይቆጠር ነበር። ይህ ፈሳሽ ከቁስል የሚወጣ ንፍጥ ወይም መግል እንዲሁም ምናልባትም በሰውነቱ ውስጥ ካለ ህመም ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ይህ ሰው ርኩስ ነው። የሚጠቀመው ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤የነካውም ሁሉ ይረክሳል።

(ዘሌዋውያን 152-13 ተመልከቱ) ይህ መርህ ለሴትም የሚሰራ ይሆናል፡፡

የዘር ፈሳሽ መውጣትም ሰውን ያረክሳል። ይህ ከሴት ጋር የተደረገ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ውጤት ከሆነ ወንዱም ሴቲቱም ርኩስ ከመሆናቸውም በላይ በውኃ መታጠብና እስከ ማታ ድረስ ንጹሕ እስኪሆኑ ድረስ መጠበቅ ይኖርባቸው ነበር (ዘሌዋውያን 1516-18 ተመልከቱ)

 

በወር አበባዋ ወቅት አንዲት ሴት ለሰባት ቀናት እንደ ርኩስ ተቆጥራለች። በዚያ ጊዜ እሷን የሚነካ ወይም የተቀመጠችበት ወይም የምትተኛበት ነገር ሁሉ እንዲሁ ርኩስ ይሆናል (ዘሌዋውያን 1519-30 ተመልከቱ)

 

የሙሴ ሕግ አንዲት ሴት ልጅ ስትወልድ እያገገመችም ቢሆንም እንኳን ርኩስ እንደሆነች ይናገራል። ልጁ ወንድ ከሆነ 40 ቀናት ርኩስ ትሆናለች፡፡ የተወለደችው ልጅ ሴት ከሆነች እናቲቱ 80 ቀናት ርኩስ ትሆናለች (ዘሌዋውያን 121-8 ተመልከቱ) በዘሌዋውያን 124 ላይ በዚህ የርኩሰት ጊዜ ሴቲቱ ወደ እግዚአብሔር መቅደስ እንድትቀርብ እንደማይፈቀድላት ግልጽ ነው፡

 

4 ከደምዋም እስክትነጻ ሠላሳ ሦስት ቀን ትቀመጥ የመንጻትዋ ቀንም እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰን ነገር አትንካ፥ ወደ መቅደስም አትግባ። (ዘሌዋውያን 12)

 

እነዚህ የመንጻት ጊዜዎች ሴቲቱ በድንኳኑ ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ማገልገል ወይም ለእግዚአብሔር መባ ማምጣት እንደምትችል ይገድባል። ጌታ እሱን የሚያመልኩት (ወንድም ሆነ ሴት) በሥርዓት ንጹሕ እንዲሆኑ ይፈልግ